ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የስርዓተ ፆታ እና አካታችነት ጉዳይን የልማት ዋንኛ ምሰሶ በማድረግ እየሰራች ነው- ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት3//2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የስርዓተ ፆታ እና አካታችነት ጉዳይን የልማት እቅዷ  ዋንኛ ምሰሶ በማድረግ እየሰራች እንደምትገኝ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ልዑክ በአሜሪካ ኒው ዮርክ ሥርዓተ-ፆታ እኩልነት እና ሴቶች ልማት አስመልክቶ እየተካሄደባለው 69ኛው አለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል።


ከጉባኤው ጎን ለጎን በዓለም አቀፉ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት/NUIDO/ እና በኦስትሪያ መንግስት የጋራ ትብብር በ'ሴቶችና አረንጓዴ ፈጠራ' /Women and Green Innovation/ ዙሪያ ለመምከር ያለመ የጎንዮሽ መድረክ (Side Event) ተካሄዷል። 


የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)  በመድረኩ ላይ በቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል።


ሚኒስትሯ በመልዕክታቸው፥ ኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግና በኢነርጂ መስክ ትልቅ እርምጃ እየወሰደች እና የኢንዱስትሪ ሽግግር ለማድረግ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።


እየተተገበሩ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና የረጅም ጊዜ የልማት እቅዶች በዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን አመልክተዋል።


የ10 አመቱ የልማት እቅድ ፈጠራን ማዕከል ያደረገ ዘላቂና አስተማማኝ ኢኮኖሚ ለመገንባት ግብ ሲያስቀምጥ የስርዓተ ፆታ እና አካታችነት ጉዳይ ዋነኛ ምሰሶ ማድረጉንም ጠቅሰዋል።


ዘላቂ የኢንዱስትሪ ሴክተር ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ያለ ሴቶች የተሟላ ተሳትፎ እውን ማድረግ አዳጋች ነው ብለዋል ሚኒስትሯ።


የኢትዮጵያ ሴቶች ከጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ስራዎች አንስቶ በፈጠራ የታገዘ የግብርና የጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ውስጥ በመሰማራት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ ድርሻ እያበረክቱ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


ሴቶች የኢንዱስትሪ ውጤቶች ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን ግንባር ቀደም የፈጠራ ባለቤት፣ ውሳኔ ሰጪና የመሪነት ሚና እንዲኖራቸው ማስቻል ይገባልም ነው ያሉት።


የኢንዱስትሪ ፖሊሲዎች አካታችና ከስርዓተ ፆታ እኩልነት ግቦች ጋር በሚገባ ማስተሳሰር ብሎም ለሴት ስራ ፈጣሪዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ መደገፍና ማበረታታት እንዳለባቸው አመልክተዋል።


እንዲሁም በቴክኖሎጂ አመንጪ፣ አቅራቢና ተጠቃሚዎች መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባም ገልጸዋል።


ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ለውጥኖች ስኬት መንግስታት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችና የግሉ ሴክተር በቅንጅትና በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም