የኩባና ኢትዮጵያ ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል - የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር - ኢዜአ አማርኛ
የኩባና ኢትዮጵያ ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል - የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2017(ኢዜአ)፡- የኩባ እና የኢትዮጵያ ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት በብዙ ዘርፎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሩኖ ኤድዋርዶ ሮድሪጌዝ ፓሪላ ገለፁ።
በ1960ዎቹ መጨረሻ የዚያድ ባሬ ኃይል በኢትዮጵያ ላይ ያወጀውን ግልፅ ወረራ ለመመከት 163 የኩባ ወታደሮች ከኢትዮጵያውያን ጎን ተሰልፈው መስዋዕትነት መክፈላቸው ይታወሳል።
መስዋዕትነት ለከፈሉ ወታደሮችም በኢትዮ-ኩባ የወዳጅነት ፓርክ የመታሰቢያ ሃውልት ቆሞላቸዋል።
በጋራ የመስዋዕትነት ታሪክ ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያና የኩባ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት 50 ዓመት አስቆጥሯል።
በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሩኖ ኤድዋርዶ ሮድሪጌዝ ፓሪላ የተሰዉ ወታደሮችን ለመዘከር በኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ፓርክ የአበባ ጉንጉን አኑረዋል።
ብሔራዊ ቤተ-መንግሥትንም ጎብኝተዋል።
ሚኒስትሩ የኩባ ታሪካዊ ወዳጅ ሀገር ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ ሲመጡ በተደረገላቸው አቀባበል መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት በጋራ መስዋዕትነት ላይ የተመሰረተ ታሪካዊ እና ረጅም ዘመናትን የተሻገረ መሆኑን ተናግረዋል።
የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገውን የሀገራቱን ትብብር ወደ ላቀደ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰራም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በሳይንስ፣ በትምህርት እና በባህል ትልቅ አቅም እንዳላቸው በማንሳት በዘርፎቹ ያላቸውን ትብብር አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።