የ1 ሺህ 446ኛው የሐጅና ዑምራ ጉዞ የምዝገባ ጊዜ ተራዘመ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3//2017(ኢዜአ)፦ የ1 ሺህ 446ኛው የሐጅና ዑምራ ጉዞ የምዝገባ ጊዜ እስከ መጋቢት 20 ቀን 2017 ዓ.ም መራዘሙን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታውቋል።

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝደንት ሸይኽ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ከጥር 15 2017 ጀምሮ ሲሰጥ የቆየው የሀጅ ምዝገባ አገልግሎት የሳውዲ አረብያ ሀጅ ሚኒስቴር ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ መሰረት የካቲት 21 ተጠናቆ እንደነበር አስታውሰዋል።

የመመዝገቢያ ጊዜው ማጠሩን ተከትሎ ሳይመዘገቡ የቀሩ አማኞች በመኖራቸው የሀጅና ኡምራ አብይ ኮሚቴ ጉዳዩን ለሳወዲ አረቢያ ሀጅ ሚኒስቴር አቅርቦ ምላሽ እንዲሰጠው ስለማስደረጉም አንስተዋል።

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንትና የሀጅና ዑምራ ዘርፍ ተጠሪ ሸይህ አብዱልዓዚህ አብዱልወሌ በበኩላቸው የሳውዲ አረቢያ የሀጅ ሚኒስቴር በርካታ የአሰራር ለውጦችን በማድረጉ የምዝገባ ጊዜው ሊያጥር ችሏል ብለዋል።

በዚሁ መሰረት ምዝገባው እስከ መጋቢት 20 ቀን 2017 ዓ.ም መራዘሙን ተከትሎ የሙስሊሙ ማህበረሰብ በተሰጠው የጊዜ ገደብ እንዲመዘገብ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም