ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት አስር ቀናት በርካታ የበልግ አብቃይ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2017(ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት አስር ቀናት በርካታ የበልግ አብቃይ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በሚቀጥሉት አስር ቀናት በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት በደቡብ፣ ደቡብ ምስራቅ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የርጥበት መጠንና የደመና ሽፋን መጨመር እንደሚኖር አስታውቋል።

በተለይ በበልግ አብቃይ አካባቢዎች በሚፈጠሩ ጠንካራ የደመና ክምችቶች በመጠንም ሆነ በሥርጭት የተሻለ ዝናብ እንደሚኖር የአየር ትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ኢንስቲትዩቱ ገልጿል።

ከተያዘው ወር አጋማሽ በኋላ የሰሜን ምሥራቅ፣ የምስራቅ፣ ደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመጠንም ሆነ በስርጭት የተስፋፋና የተጠናከረ ዝናብ እንደሚያገኙ ጠቁሟል።

የሚኖረው የዝናብ መጠንና ስርጭት የበልግ የግብርና ስራዎችን ለማከናወን ከፍተኛ ጠቃሜታ እንዳለውም ተመላክቷል።

በደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ በመካከለኛው፣ በሰሜን ምስራቅ፣ በምስራቅ እንዲሁም በስምጥ ሸለቆና አጎራባች አካባቢዎች የተሻለ ጥንካሬ ይኖራቸዋልም ነው ያለው።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የደቡብ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ሶማሌ፣ አማራ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ጋምቤላ፣ አዲስ አበባ፣ ሀረሪ እና ድሬዳዋ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙም የትንበያ መረጃው አመላክቷል።

በትንበያው መሰረት በወሩ አጋማሽ በጋምቤላ፣ በአፋር፣ በሶማሌ፣ በቤንሻንጉል-ጉሙዝ እና በምዕራብ አማራ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ሙቀት እንደሚመዘገብ ይጠበቃል በሏል።

የሚኖረው የዝናብ ሁኔታ የአፈር ውስጥ የውሃ መጠንን በመጨመር ለማሳ ዝግጅት፣ ለቋሚ ተክሎች እንዲሁም ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት በጎ ጎን እንዳለውም ተመላክቷል።

በአባይ፣ በኦሞ ጊቤ፣ በአዋሽ፣ በስምጥ ሸለቆ፣ በባሮ፣ በዋቤ ሸበሌ፣ ተከዜ፣ አፋር ደናክል ተፈሰሶች ላይ የተለያየ ደረጃ ያለው ርጥበት እንደሚኖር ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም