አራተኛው ዙር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስራ በይፋ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
አራተኛው ዙር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስራ በይፋ ተጀመረ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2017(ኢዜአ)፡- አራተኛው ዙር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስራ በይፋ መጀመሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሳውዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ከ1 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ዛሬ ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡
ተመላሾቹን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው አቀባበል አድርገውላቸዋል።
አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በዚሁ ወቅት፤ አራተኛው ዙር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስራ በይፋ መጀመሩን ተናግረዋል።
በዚህም ከዛሬ ጀምሮ በሳምንት ዘጠኝ በረራዎችን በማድረግ ዜጎችን የመመለስ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ዜጎቹን የመመለስ ተግባር የመንግሥት የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ አካል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)፤ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ዜጎችን የመመለስ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡
ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ዜጎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ መሆናቸውን ጠቁመው ዜጎቹ በሀገር ልማትና ዕድገት እንዲሳተፉ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በዛሬው ዕለት 43 ዜጎች ከማይናማር መመለሳቸውም ይታወቃል።