ቀጥታ፡

በክልሉ የመድኃኒት አቅርቦት የተቀላጠፈ እንዲሆን የሚያስችሉ አሰራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው

መቀሌ፤ መጋቢት 3/2017 (ኢዜአ) ፡-በትግራይ ክልል  የመድኃኒት አቅርቦት የተቀላጠፈ እንዲሆን የሚያስችሉ አሰራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑ ተገለጸ።

የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት በጋራ ባዘጋጁት የቪዲዮ ኮንፈረንስ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በውይይቱም አዳዲስ የመድኃኒት አቅርቦት አሰራርና ኢኒሺዬቲቮችን በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል። 

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ፤ የመድኃኒት አቅርቦትን ለማሳለጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ አዳዲስ አሰራሮች አስመልክተው ገለፃ አድርገዋል። 

በዚሁ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሄዋን ሰመረን ኢዜአ አነጋግሯል።

የውይይቱ ዓላማ አዳዲስ አሰራሮች እና የአቅርቦት ሰረግ አቅርቦትና ፍላጎትን በማመጣጠን የተሻለ እና ውጤታማ ስራ ለማከናወን ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በሃላፊዎቹ ማብራሪያ ተሰጥቷል ብለዋል።

ኮሚትድ ዲማንድ ኢኒሺዬቲቭ የተሰኘው የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት የህዝብና የተገልጋይ ቁጥርን ከግምት ያስገባ በመሆኑ አገልግሎቱን የሚያሻሽለው መሆኑንም ተናግረዋል። 

የጤና ተቋማት የዲጂታል አሰራር ኢኒሺዬቲቭ የመድኃኒት ስርቆትና ብክነትን በመከላከል የስርጭት እና የቁጥጥር ስርዓቱን በማዘመን ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ እንደሆነም አመልክተዋል። 

በትግራይ ክልል የሚገኙ የጤና ተቋማት አመራሮች እና የፋርማሲ ባለሙያዎች በመድረኩ የተሳተፉ ሲሆን፣ በቀጣይም ከጤና ሚኒስቴር እና ከአገልግሎቱ ጋር በመተባበር አሰራሮቹን ተግባራዊ በማድረግ የክልሉን የመድኃኒት አቅርቦት ለማሻሻል ይሰራል ብለዋል። 

በኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የመቀሌ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የመድኃኒት ቁጥጥር አስተባባሪ መሀመድ ከይሩ፤ ለ182 የጤና ተቋማት ፅህፈት ቤቱ መድኃኒት እያከፋፈለ መሆኑን ገልፀዋል።

አሁን ላይ የጤና ተቋማቱ የመድኃኒት አቅርቦት አቅም 75 በመቶ መድረሱንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም