ቀጥታ፡

የትራንስፖርት ዘርፉ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ወሳኝ ነው - የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2017(ኢዜአ)፡- የትራንስፖርት ዘርፉ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ወሳኝ በመሆኑ ለስኬታማነቱ ዘርፉን የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሀገሪቱን የአረንጓዴ ልማት እንደሚያሳልጥ በታመነበት የኤሌክትሪክና ታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች ማስፈፀሚያ ረቂቅ ስትራቴጂ ላይ ውይይት ተደርጓል።


 

ስትራቴጂውን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በጋራ ያዘጋጁት መሆኑ ተገልጿል፡፡

በውይይቱ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር)፣ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ ሚኒስትር ዴኤታዎችና ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በዚሁ ወቅት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሰራች ትገኛለች።

የትራንስፖርት ዘርፉ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ ለስኬታማነቱ ዘርፉን የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በዓመት ለነዳጅ ግዢ ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደምታወጣ አውስተው፤ ታዳሽ ሃይል የአየር ብክለትን ከመቀነስ ባለፈ ለነዳጅ የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ ለሌሎች መሰረተ ልማቶች ግንባታ ማዋል እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ከተሞችን ፅዱና ስማርት ለማድረግ የጎላ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፤ ለዚህ ደግሞ የኤሌክትሪክና ታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎችን በብዛት ማቅረብ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ስትራቴጂው የሀገር ውስጥ አምራቾችን የሚያበረታታና የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግርን ለማምጣት ብሎም የስራ እድል መፍጠር የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።

የነዳጅ ተሽከርካሪዎች የሚያስከትሉትን የአየር ብክለት ለመቀነስ የሚረዳ ቴክኖሎጂ መተግበር የሚያስችል ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

መድረኩ የኤሌክትሪክና ታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች ማስፈፀሚያ ረቂቅ ስትራቴጂ ላይ ከመወያየት ባለፈ ወደ ተጨባጭ ስራ መግባት የሚያስችል መሆኑንም አስታውቀዋል።


 

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ያለው የኢኮኖሚ እድገት፣ የህዝብ ብዛት እንዲሁም የከተሞች መስፋፋት የትራንስፖርት ፍላጎት እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል።

በሀገር ውስጥ ያለው የታዳሽ ኃይል አቅም ለዘርፉ ምቹ ገበያ የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመው፤ የኤሌክትሪክና ታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች ማስፈፀሚያ ስትራቴጂ ማዕቀፍ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘርፉ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የፋይናንስ አቅርቦትና የተለያዩ ማበረታቻዎችን ለማጠናከር እንደሚሰራም ተናግረዋል።


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ስትራቴጂው በትራንስፖርት ዘርፉ ታዳሽ ሀይልን ለመጠቀም ልዩ እድል የፈጠረ ነው።

ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ለማድረግ እንዲሁም የባትሪ መሙያ መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በስትራቴጂው ላይ የስትሪንግ ኮሚቴ አባላት ውይይት አድርገው የፀደቀ ሲሆን፤ በአንድ ወር ውስጥ የሚመለከታቸው አካላት ስትሬቴጂውን መተግበር የሚያስችል እቅድ ማውጣት እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም