ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከጃማይካ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት- አምባሳደር አየለ ሊሬ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከጃማይካ ጋር ያላትን ለረጅም ጊዜ የቆየ የሁለትዮሽ ትብብር አበክራ እንደምትሰራ በጃማይካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት አየለ ሊሬ ገለጹ።

አምባሳደር አየለ ሊሬ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለጃማይካ መንግስት ዋና ተጠሪ ሰር ፓትሪክ ሊንተን አለን፣ የሹመት ቅጂ ደብዳቤያቸውን ደግሞ ለጃማይካ የውጭ ጉዳይ እና የወጪ ንግድ ሚኒስትር ሴናተር ካሚና ጆንሰን ስሚዝ አቅርበዋል።

ከኢትዮጵያ መንግስት መሪዎች የተላከውን የሰላምታ እና የመልካም ምሾት መግለጫ መልዕክት ለጃማይካ መንግስት ባለስልጣናት አድርሰዋል።

አምባሳደሩ የኢትዮጵያ እና ጃማይካን የሁለትዮሽ ትብብር እና አጋርነት ለማጠናከር አበክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የጃማይካ መንግስት ዋና ተጠሪ ሰር ፓትሪክ ሊንተን አለን፥ አምባሳደሩ የሁለቱን ሀገራት ትብብር ለማጠናከር ለሚያድርጉት ጥረት መንግስታቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ እና ጃማይካ ለረጅም ጊዜ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው በኩባ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዳላቸው አመልክቷል።ሃቫና ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጃማይካን ሸፍኖ ይሰራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም