ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ በቁርጠኝነት እየሰራች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ በቁርጠኝነት እየሰራች ነው
አዲስ አበባ፤መጋቢት 3/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ በቁርጠኝነት እየሰራች እንደምትገኝ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ገለጹ።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ያዘጋጀው 57ኛው አህጉራዊ የኢኮኖሚ ልማት፣የገንዘብና የፕላን ሚኒስትሮች ጉባኤ በባለመያዎች ደረጃ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው፥ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት የአፍሪካዊያን የጋራ ርዕይ ነው ብለዋል።
የነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነቱም የአፍሪካን የኢኮኖሚ ነፃነት በማፋጠን፣ የጋራ ብልጽግናን እውን በማድረግ እና ጠንካራ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን ለማሳለጥ የማይተካ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራን ለማፋጠን የጋራ ጥረት ትብብርና ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።
ለዚህም ሀገራት የመሰረተ ልማት ትስስር የሚያሳልጡ የመሰረተ ልማት ግንባታ ኢንቨስትመንትን በማሳደግ የንግድ ፖሊሲ፣የጉምሩክ ሂደትና የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅቶች ላይ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ በቁርጠኝነት እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
ለአብነትም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ በመንገድ ግንባታ፣በባቡር ትራንስፖርት፣በኤሌክትሪክ ኃይል ቀጣናዊ ትስስርን በመፍጠር ለአሕጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ ስኬታማነት የላቀ ሚና እየተወጣች ነው ብለዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርክና በልዩ የኢኮኖሚ ዞን ልማት ኢንቨስትመንት በመሳብ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን በማሳደግ ለአፍሪካ የንግድና ኢኮኖሚ ትስስር እየሰራች መሆኗን ጠቅሰዋል።
በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ምክትል ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ፔድሮ፥ የአፍሪካ ሀገራት ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነቱን የሚያሳልጡ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ማቀላጠፍ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የባለሙያዎች ጉባዔ “የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራን ማፋጠን፤አፈጻጸሙን የሚያልቁ ስትራቴጂካዊ እርምጃዎችን መቀየስ” በሚል መሪ ሀሳብ እስከ መጋቢት 5/2017 ዓ.ም ይቆያል።