ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በክልሉ የኢንዱስትሪ ዘርፉን በማነቃቃት ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው

ሆሳዕና፣መጋቢት 3/2017(ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኢንዱስትሪ ዘርፉን በማነቃቃት ጉልህ ሚና መጫወቱን የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

"በላቀ ጥራትና ምርታማነት ወደ ሁለንተናዊ ብልፅግና ተምሳሌትነት" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በምስራቅ ጉራጌ ዞን ቡኢ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

የቢሮው ኃላፊ አባስ መሀመድ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፣በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በርካታ የተዘጉና በችግር ውስጥ የነበሩ ኢንዱስትሪዎች በአዲስ መልክ ስራ እንዲጀምሩ ከማድረግ በተጨማሪ ተኪ ምርት እንዲያመርቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

ንቅናቄው የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ከማሳደግ በሻገር የምርት ጥራትና ፍጥነት እንዲሻሻልም እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል።

ቢሮው የኢንዱስትሪ ዘርፉን ወደ ገጠር በማስፋት የማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

በክልሉ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመረዳት በዘርፉ ከሚመነጨው ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን ባለሀብቶች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዛሬ በአምስት ቢሊየን ብር ካፒታል በቡኢ ከተማ የግንባታ ስራው የተጀመረው የችፑድ ፋብሪካ የገጠሩን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)ና የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ስርሞሎን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና በተለያየ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች እየተሳተፉ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም