ቀጥታ፡

ተቋማቱ በጥራት ማረጋገጫ ዘርፍ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 2/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት እና የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በጥራት ማረጋገጫ ዘርፍ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር መዓዛ አበራ (ኢ/ር) እና የዩኒቨርሲቲው የምርምር እና ቴክኖሎጂ ምክትል ፕሬዝዳንት አብርሃም ደበበ (ዶ/ር) ናቸው።

የጋራ መግባቢያ ስምምነቱ ተቋማቱ በሰው ሀብት አቅም ግንባታ እና ልማት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የልማት መስኮች እና በጥራት ማረጋገጫ ዘርፍ በትብብር መስራት የሚያስችላቸው ነው።

ስምምነቱ ድርጅቱ በጥራት ማረጋገጥ ዘርፍ የልዕቀን ማዕከል ለመሆን የያዘውን ለማሳካት የሚያስችላው ወሳኝ እርምጃ መሆኑ ተገልጿል።

መዓዛ አበራ (ኢ/ር) የጋራ ትብብርን የሚያጠናክሩ ስምምነቶች ስራን ውጤታማ እንደሚያደርጉ መግለጻቸውን ከድርጅቱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም