ኢትዮጵያ እና አውሮፓ ህብረት ትብብራቸውን የበለጠ ለማሳደግ መጪው ጊዜ ብሩህ ነው-አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ኢመስበርገር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና አውሮፓ ህብረት ትብብራቸውን የበለጠ ለማሳደግ መጪው ጊዜ ብሩህ ነው-አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ኢመስበርገር
አዲስ አበባ፤መጋቢት 2/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እና አውሮፓ ህብረት ትብብራቸውን የበለጠ ለማሳደግ መጪው ጊዜ ብሩህ መሆኑን በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ኢመስበርገር ገለጹ።
የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ኢመስበርገር የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት የ50 ዓመታት ግንኙነትን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ አጋሮች መካከል አንዷ ሆና መቀጠሏን ጠቅሰው፥ከኢትዮጵያ ጋር ባሉ ትብብሮች አማካኝነት በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ህብረቱ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የነበረው ግጭት በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት መፈታቱንና በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን የሰላም ተግባራትን በንቃት እንደሚከታተልና እንደሚደግፍ አመልክተዋል።
የሰላም ሂደቱን ጨምሮ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ በፍጥነት መንቀሳቀሱን አብራርተው፥ ትጥቅ ለማስፈታት፣ለሽግግር ፍትህ እና ለአገራዊ ምክክርም ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ህብረቱ በመንግስት የተጀመሩ የሪፎርም እና የለውጥ ስራዎች እንዲሳኩ የሚፈልጋቸው አጀንዳዎች መሆናቸውን ገልጸው፤ ከነዚህም ግብርና፣ የአረንጓዴ አሻራ እና ዲጂታላይዜሽን ትልቅ የለውጥ አጀንዳዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ እና አውሮፓ የባህል እና ትምህርታዊ ልውውጦችን በመገንባት ላይ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ገልጸው፤ግንኙነቱን ለማጠናከር የሚያግዙ በርካታ ስኮላርሺፖች መሰጠታቸውን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በየዓመቱ በአውሮፓ እየተማሩ ግንኙነቱን ለማጠናከር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የህብረቱ አባል ሀገራት በስፖርት፣በሙዚቃ፣በጥበባት፣በፊልም ፌስቲቫሎች እና በመሳሰሉት ያላቸው ግንኙነት ከፍ እያለ መምጣቱንም ጠቁመዋል።
የአውሮፓ ህብረት እና ኢትዮጵያ ትብብራቸውን የበለጠ ለማሳደግ መጪው ጊዜ ብሩህ መሆኑንም አመላክተዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ እና አሜሪካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል አብርሀም መንግስቱ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያና አውሮፓ ህብረት ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
በተለያዩ መስኮች ያሉ ትብብሮች ጠንካራ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የተገበረችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለአውሮፓውያን ድርጅቶች ሰፊ እድል ማምጣቱን ጠቁመዋል።