የኢትዮጵያና የካዛኪስታን የሁለትዮሽ ግንኙነት ከፍተኛ ዕድገት አስመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና የካዛኪስታን የሁለትዮሽ ግንኙነት ከፍተኛ ዕድገት አስመዝግቧል
አዲስ አበባ፤መጋቢት 2/2017(ኢዜአ)፦ባለፉት አሥር ዓመታት የኢትዮጵያና የካዛኪስታን የሁለትዮሽ ግንኙነት ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ መምጣቱን ተሰናባቹ የካዛኪስታን አምባሳደር ገለጹ፡፡
የቀድሞው የካዛኪስታን አምባሳደር ባርሊባይ ሳዲኮቭ በኢትዮጵያ በነበራቸው የአምስት ዓመታት ቆይታ ሁሉንም የአገሪቱ አካባቢዎች በመጎብኘት ኢትዮጵያ ታላቅ ታሪክ እንዳላት መረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ የአገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር መሥራታቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ባለፉት አሥር ዓመታት የኢትዮጵያና የካዛኪስታን የሁለትዮሽ ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ ዕድገት ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡
አገራቱ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ ፣ በንግድ ፣ በኢንቨስትመንት እንዲሁም በባህል ልውውጥ ያላቸውን ግንኙነት የሚያጠናክሩ ፍኖተ ካርታዎች ተዘጋጅተው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ የንግድ ልዑካን እኤአ በ2023 በካዛኪስታን በነበረው ቆይታ በአስታና አለም አቀፍ ፎረም ላይ መሳተፉን አስታውሰዋል፡፡
ልዑኩ ከካዛኪስታን የመንግስት ባለስልጣናት እና ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጉን ተከትሎ አገራቱ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችላቸውን መሰረት መጣላቸውን ተናግረዋል፡፡
ካዛኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደምትሰራ አረጋግጠዋል፡፡
ካዛኪስታን እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2014 ኤምባሲዋን በኢትዮጵያ መክፈቷ ይታወቃል፡፡