ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ከቻይና ኢነርጂ ዓለም አቀፍ ግሩፕ ፕሬዝዳንት ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ከቻይና ኢነርጂ ዓለም አቀፍ ግሩፕ ፕሬዝዳንት ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 2/2017(ኢዜአ)፦ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር ኢ/ር) ከቻይና ኢነርጂ ዓለም አቀፍ ግሩፕ ፕሬዝዳንት ቺያዎ ሽዩቢን ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ሚኒስትሩ የቻይና ኢነርጂ ዓለም አቀፍ ግሩፕ ከዋና የኤሌክሪክ መስመር ርቀው የሚገኙ አካባቢዎች ላይ የኦፍግሪድ የፀሐይ ኃይል ተደራሽ ማድረግ፣ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ማሻሻል፣ የኃይል ማሰራጫና ማከፋፈያ መሰረተ ልማቶች፣ የከርሰ ምድር ውሃ ፍለጋና የቁፋሮ ስራዎች እንዲሁም አጠቃላይ የሳኒቴሽንና የፍሳሽ ማጣሪያ መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ መሰማራት እንደሚችል ገልጸዋል።
በሚኒስቴሩ የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሡልጣን ወሊ(ዶ/ር ኢ/ር) በኢትዮጵያ ከፍተኛ የታዳሽ ኃይል የማመንጨት አቅም መኖሩን ነገር ግን የኤሌክትሪክ ተደራሽነቱ ከ54 በመቶ ያልበለጠ ነው ብለዋል፡፡
የመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ፖሊሲ በኢነርጂ ልማት ለመሰማራት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አመልክተዋል።
የቻይና ኢነርጂ ዓለም አቀፍ ግሩፕ ፕሬዝዳንት ቺያዎ ሽዩቢን ተቋማቸው በኢነርጂ ልማት ዘርፍ እንዲሁም በቻይና እና በአፍሪካ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የመገንባት ልምድ እንዳለው መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።