የአብሮነት እሴትን የሚሸረሽሩ መረጃዎችን የሚያስተላልፉ ግለሰቦች በህግ ሊጠየቁ ይገባል - የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ - ኢዜአ አማርኛ
የአብሮነት እሴትን የሚሸረሽሩ መረጃዎችን የሚያስተላልፉ ግለሰቦች በህግ ሊጠየቁ ይገባል - የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 2/2017(ኢዜአ)፡-በማህበራዊ የትስስር ገጾች ሃይማኖትንና የአብሮነት እሴትን የሚሸረሽሩ አሉታዊ መረጃዎችን የሚያስተላልፉ ግለሰቦችን ማውገዝና በህግ ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በሰጡት መግለጫም የማህበረሰቡን የሰላም እና የአብሮነት እሴቶችን ሊጎዱ የሚችሉ አንዳንድ ኢ- ሃይማኖታዊና አሉታዊ መረጃዎች በማህበራዊ የትስስር ገጾች የማስተላለፍ ድርጊቶች እየተስተዋሉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሁሉም ሃይማኖቶች አስተምህሮ ሰላም፣ መተባበርና ወንድማማችነትን እንደሚሰብክ አመልክተው፤ ከሃይማኖቶቹ አስተምሮ ውጭ የሚደረጉ ተግባራት ተቀባይነት የሌላቸው ብቻ ሳይሆኑ የሚወገዙ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት የሚተላለፉ አሉታዊ መረጃዎችና የአብሮነትን እሴት የሚጎዱ ተግባራት በወንጀል የሚያስጠይቁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዝሀ ሀይማኖት መገኛና መኖሪያ መሆኗን ያመለከቱት ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የትኛውንም ዓይነት የሃይማኖት ተቋማትን፣ አስተምህሮትና መገለጫዎቻቸውን የሚያጥላሉ ንግግሮችን በጽኑ ያወግዛል ብለዋል።
እነዚህን አሉታዊ እንቅስቃሴዎች እና መልዕቶች በማውገዝ ለዘመናት የዘለቀውን ሰላም እና አብሮነት ይበልጥ አጠንክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
አማኞች በነዚህ አሉታዊ መረጃዎች ሳይደናገሩ የጾም፣ ጸሎትና የንስሀ ተግባራቸውን መቀጠል እንዳለባቸው ነው ጉባኤው የገለጸው።
በማህበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ተጽእኖ ያላቸውን መረጃዎች የሚያስተላልፉ፣ አብሮነትና መከባበርን የሚያውኩ ሕገ-ወጥ ግለሰቦችና ቡድኖች ከድርጊታቸው እንዲታረሙ የሕግ አስከባሪ አካላትም ሕግና ሥርዓት እንዲጠበቅ እንዲያደርጉ ጉባኤው ጥሪ አቅርቧል።