ቀጥታ፡

ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ከግማሽ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስኳር አምርቷል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 2/2017(ኢዜአ)፡- የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ በ2017 በጀት ዓመት እስከ አሁን ከ500 ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር ማምረቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አስታወቀ።

ፋብሪካው የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ(ዶ/ር)፣ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አወሉ አብዲ እና የተቋሙ አመራሮች የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።


 

ጉብኝቱ የተቋሙን አፈጻጸም መገምገምና የመሰረተ ልማት አቅሙን መፈተሽ እንደሆነ ተገልጿል።

የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ በ2017 በጀት ዓመት እስከ አሁን ከ500 ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር ማምረቱን ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ይህም ፋብሪካው በበጀት ዓመቱ ማብቂያ ለማምረት ያቀደውን የአንድ ሚሊዮን ኩንታል ስኳር እቅድ ለማሳካት በትክክለኛ መስመር ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ፋብሪካው ከዋና ምርቱ በተጓዳኝ የግብርና ምርቶችን በማምረት ለሰራተኞቹ እና ለአካባቢው ማህበረሰብ እንቁላል፣ አሳ እና አትክልቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አመራሮች ኩባንያው በግብርናው መስክ እያሳየ ያለው ለውጥ፣ የሜካናይዜሽን አጠቃቀምን በማሳደግ፣ የእርሻ ስራዎችን በማስፋፋት፣ በአቅም ግንባታ እና ስትራቴጂካዊ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመጠቀም እያስመዘገበ ያለው ውጤት መልካም እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢንቨስትመንት ተቋሙ ፋብሪካው የያዘው የዘላቂ እድገት ውጥን እንዲሳካ ድጋፍ እንደሚያደርግ መገለጹም በመረጃው ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም