ቀጥታ፡

በማስፋፊያ ሥራ ተጨማሪ 310 ሜጋ ዋት ኃይል ማግኘት ተችሏል - የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 2/2017(ኢዜአ)፡- ባለፉት አምስት ዓመታት በማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ በተከናወኑ የማስፋፊያ ስራዎች ተጨማሪ 310 ሜጋ ዋት ኃይል ማግኘት መቻሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አስታወቀ።

የተቋሙ የሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ጋሻው እንድሪያስ እንዳሉት በከተሞችና በኢንዱስትሪ መስፋፋት ምክንያት ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት ተፈጥሯል።


 

ለፍላጎቱ ምላሽ ለመስጠት ከአዳዲስ የኃይል መሰረተ ልማት ግንባታዎች በተጨማሪ በነባር ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የአቅም ማሳደግ፣ የማስፋፊያ እና ማዘመን ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

የማከፋፈያ ጣቢያዎች ዕድሜ፣ የኃይል ጭነት ከመጠን በላይ መሆን እና በጣቢያዎች ላይ በሚከሰቱ ድንገተኛ ችግሮች በዕቃዎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ለአቅም ማሳደግ እና ማሻሻያ ሥራዎች መከናወን ምክንያት መሆናቸው ተገልጿል።

እንደ አቶ ጋሻው ገለጻ ባለፉት አምስት ዓመታት በነባር ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ 22 የኃይል ትራንስፎርመሮችን በመትከል 310 ሜጋ ዋት ተጨማሪ ኃይል ማግኘት ተችሏል።


 

ቦሌ ለሚ፣ ሻሸመኔ፣ ጂግጂጋ፣ በደሌ፣ ሐረር ሁለት እና ሶስት፣ ወልቂጤ፣ ደብረ ታቦር፣ ጊንጪ፣ ደብረ ብርሃን፣ ድሬዳዋ ሁለት እና ሶስት፣ አሸጎዳ፣ ገላን፣ ሆሳዕና፣ ባህርዳር ሁለት፣ ጌዶ እና ጋሸና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የአቅም ማሳደግ፣ ማስፋፊያ እና የማዘመን ሥራዎች ከተከናወኑባቸው መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም