የኢትዮጵያ መድን እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መድን እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ
አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 2/2017 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ22ኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ውሎ የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ከአምናው የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ መድን በ38 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ28 ነጥብ 9ኛ ደረጃን ይዟል።
መድን የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ያጠናክራል። በአንጻሩ ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድል ከቀናው ወደ መሪዎቹ ጠርታ መጠጋት የሚችልበትን እድል ያገኛል።
ቡድኖቹ በሊጉ በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ መለያየታቸው ይታወሳል።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ ወላይታ ድቻ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ይጫወታሉ።
ወላይታ ድቻ በ30 ነጥብ 6ኛ ደረጃን ይዟል። ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ9 ነጥብ የመጨረሻውን 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ወላይታ ድቻ 2 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረጉ የ22ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ባህር ዳር ከተማ ሀድያ ሆሳዕናን 1 ለ 0 ሲረታ ሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል።