በራስ አቅም የልማት ስራዎችን መደገፍ የሚያስችል እንቅስቃሴ እያደረግን ነው - የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች - ኢዜአ አማርኛ
በራስ አቅም የልማት ስራዎችን መደገፍ የሚያስችል እንቅስቃሴ እያደረግን ነው - የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 1/2017(ኢዜአ)፡- ከውጭ ድጋፍ በመላቀቅ በራስ አቅም የልማት ስራዎችን መደገፍ የሚያስችል እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ገለፁ።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አዋጅ ቁጥር 1113/2011 ማንኛውም ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ለያዘው ዓላማ መሳካት ከየትኛውም ሕጋዊ ምንጭ ገንዘብ የመጠየቅ፣ የመቀበልና የመጠቀም መብት እንዳለው ይደነግጋል።
ለዓላማው መሳካት ገቢ ለማግኘት በማንኛውም ሕጋዊ የንግድና ኢንቨስትመንት ሥራ ውስጥ አግባብነት ባላቸው የንግድና ኢንቨስትመንት ሕጎች መሠረት የመሳተፍ መብት እንዳለውም ያብራራል።
የክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ድርጅቶች ህብረት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ንጉሱ ለገሰ ለኢዜአ እንዳሉት በህብረቱ ስር ያሉ ከ400 በላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተለያዩ የልማት ስራዎችን እየደገፉ ይገኛሉ።
ህብረቱ በስሩ ያሉ ድርጅቶች በራስ አቅም ገቢ በማመንጨት የልማት ስራዎችን መደገፍ እንዲችሉ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሥነ ሕዝብ፣ ጤና እና አካባቢ ጉዳዮች ጥምረት ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳሻው ሞገሴ ጥምረቱ በስሩ ላሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተቀናጀ አሰራርን የማስተዋወቅና የመደገፍ ዓላማ ይዞ የተቋቋመ ነው ብለዋል።
በጥምረቱ ስር ያሉ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንደ ሀገር የተያዙ እንደ ሌማት ትሩፋት፣ የስራ እድል ፈጠራና አረንጓዴ አሻራ ያሉ የልማት ስራዎች ላይ እየተሳተፉና እየደገፉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የበጎ ፍቃደኝነትን ባህል ማዳበር፣ የግል ዘርፉን ተሳትፎ በማጠናከርና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እርስ በርስ መደጋገፍ ባህልን በማሳደግ ለሀገር የበለጠ አስተዋፅኦ ማበርከት እንዲችሉ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ በመሰማራት የራስን አቅም ለማሳደግ እየሰራን ነው ያሉት ደግሞ የመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና ዳይሬክተር መሰረት አዛገ ናቸው።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የድጋፍና አገልግሎት መሪ ስራ አስፈፃሚ ኃይለስላሴ ገብረሚካኤል ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሀገር ውስጥ አቅምን ተጠቅመው ዓላማቸውን መፈፀም የሚያስችሉ አማራጮች እንዳሉ ገልፀዋል።
ከእነዚህም መካከል ህብረተሰቡን ያሳተፈ የገቢ ማሰባሰብ ስራ እና የተለያዩ የንግድ ስራዎችን ማካተት አማራጮች መሆናቸውን ተናግረዋል።