የንባብ ባህልን በማሳደግ ራሱን በእውቀት የሚገነባ ትውልድ ለመፍጠር ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የንባብ ባህልን በማሳደግ ራሱን በእውቀት የሚገነባ ትውልድ ለመፍጠር ትኩረት ተደርጓል
ጀሙ፣ መጋቢት 1/2017 (ኢዜአ)፡-የንባብ ባህልን በማሳደግ ራሱን በእውቀት የሚገነባና ለሌሎችም የሚያጋራ ትውልድ ለመፍጠር ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት አስታወቀ።
አገልግሎቱ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ጀሙ ከተማ ባዘጋጀው የንባብ ሳምንት መርሃ ግብር ግምታቸው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ማጣቀሻ መጻህፍትን ለትምህርት ቤቶች አበርክቷል።
የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻህፍት አገልግሎት የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሳው በወቅቱ እንደገለጹት፣ አገልግሎቱ በተለያዩ አካባቢዎች የህብረተሰቡን የንባብ ባህልና እውቀት ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
ትምህርት ቤቶች ትውልድን በእውቀት የሚያንጹ በመሆናቸው ከመማሪያ መጻህፍት በተጨማሪ እውቀትን የሚያስጨብጡ አጋዥ መጻህፍት እጥረት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
አገልግሎቱ ይህን ውስንነት በመሙላት ንባብን ባህል በማድረግ ራሱን በእውቀት የሚገነባና ያወቀውን ለሌሎች የሚያጋራ ትውልድ ለመፍጠር ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑንም አመልክተዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ማርቆስ ቡልቻ በበኩላቸው እንደ ክልል የአዲሱን ሥርዓተ ትምህርት የሚያግዙ መጻህፍት እጥረት መኖሩን ገልጸዋል።
ቢሮው ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር አጋዥ መጻህፍትን ለማሟላት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዛሬ የተደረገው የመጻህፍት ድጋፍ በገንዘብ የማይተመን እውቀት ለማግኘት ያስችላል ብለዋል።
ከአገልግሎቱ ዛሬ የተበረከቱት መጽሐፍት ለ12 ትምህርት ቤቶች እና ለአንድ የሕዝብ ቤተ መጻህፍት እንደሚከፋፈልም ጠቁመዋል።
የምዕራብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ኬኒ ዞኑ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የተደራጀ በመሆኑ በትምህርት ቤቶች የመጻህፍት ጉድለት መኖሩን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የቤተመዛግብትና ቤተመጻህፍት አገልግሎት በትምህርት ተቋማት ያለውን የመጻህፍት ችግር ተረድቶ ዛሬ ላደረገው የመጻህፍት ድጋፍም አመስግነዋል።
"ማንበብ በጥበብ ጎልብቶ ለማበብ" በሚል መሪ ቃል በጀሙ ከተማ በተካሄደ የንባብ ሳምንት መርሃ ግብር ንባብን ማጎልበት ያለውን ፋይዳ የተመለከተ ጽሁፍም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።