ህብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህሉን ማጎልበት አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህሉን ማጎልበት አለበት
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 1/2017(ኢዜአ)፡- ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ለመድረስ ህብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህሉን እንዲያጎለብት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ ጥሪ አቅርበዋል።
የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት በመጋቢት ወር የሚከናወነውን የደም ልገሳ ንቅናቄ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ ሚኒስቴሩ በልዩ ልዩ የጤና እክሎች ሳቢያ ደም የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ደም የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በስፋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ዜጎችን ከሞት በመታደግ ጤናማ ማህበረሰብን ለመፍጠር ወሳኝ ነው ብለዋል።
የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ደም የማግኘት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር ዜጎች ደም የመለገስ ባህላቸውን ማጎልበት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
”መጋቢት የደም ልገሳ ወር” በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ የደም ልገሳና የግንዛቤ ማስጨበጫ የንቅናቄ መርኃ ግብር እንደሚከናወን ገልጸው በዚህ ላይ ህብረተሰቡ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አሸናፊ ታዘበው(ዶ/ር) በበኩላቸው ጊዜው የአፅዋማት ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የደሞ እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡
እጥረቱን አስቀድሞ ለመከላከል በዚህ ወር ከበጎ ፈቃደኞች ደም መሰብሰብ የሚያስችል እንቅስቃሴ ይከናወናል ብለዋል።
ንቅናቄው ውጤታማ እንዲሆን ከህብረተሰቡ ባሻገር ተቋማት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የደም ልገሳ መርኃ ግብሩ በተለያዩ ግልጽ ቦታዎች በአገልግሎቱ ቅርንጫፎች እንዲሁም በአቢሲኒያ ባንክ እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡