የሐይማኖት እሴቶቻችንን ለሀገር ግንባታ ልንጠቀምባቸው ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሐይማኖት እሴቶቻችንን ለሀገር ግንባታ ልንጠቀምባቸው ይገባል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 1/2017(ኢዜአ)፡- የሐይማኖት እሴቶቻችንን ለሀገር ግንባታ ልንጠቀምባቸው ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ እየሱስ ፕሬዘዳንት ቄስ ዮናስ ይገዙ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በአዲስ አበባ በተካሔደው "መለኮታዊ ጉብኝት ለኢትዮጵያ" የስብከት፣ የጸሎት፣ የዝማሬና ምስጋና መርሃ-ግብር ላይ በርካታ የወንጌል አማኞች ታድመዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ-ክርስቲያን መካነ እየሱስ ፕሬዝዳንት ቄስ ዮናስ ይገዙ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ሰላም፣ አብሮነትና እርስ በእርስ ወዋደድ የሁሉም ሃይማኖቶች እሴቶችና አስተምህሮዎች ናቸው፡፡
እነዚህን የሐይማኖት እሴቶችና አስተምህሮዎች የእለት ከእለት እንቅስቃሴዎቻችን አካል በማድረግ ለሀገር ግንባታ ልንጠቀምባቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡
ወጥቶ መግባት፣ ሰርቶ መብላትና ወልዶ ማሳደግ የሚቻለው ሰላም ሲኖር መሆኑን በመናገር እርስ በርስ በመከባበርና በመዋደድ ለሰላም መረጋገጥ በጋራ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
የሐይማኖት እሴቶቻችንን ለሀገር ግንባታ ለመጠቀም የሀይማኖት አባቶች ትልቅ ሃላፊነት አለብን ብለዋል፡፡
ምዕመናን የሐይማኖት ተቋማትና የእምነት አባቶች የሚሰጡትን ትምህርት ተግባር ላይ በማዋል ስለ ሰላም፣ ስለ አንድነትና ስለፍቅር ልባቸውን ማቅናት አለባቸው ነው ያሉት፡፡
እየሩሳሌም ወልደ ትንሳዔ የተባለች የመርኃ ግብሩ ተሳታፊ አንድ ስንሆን ሰላምንና ዕድገትን ማስፈን እንችላለን ብላለች፡፡
ሰላማዊት አበራ በበኩሏ በሃይማኖትና በብሄር ሳንለያይ እርስ በእርስ መረዳዳት አለብን በማለት ተናግራለች፡፡
ኪሩቤል እሱ የተባለው ተሳታፊ ሁሉም ሃይማኖቶች ስለ ሰላም በብርቱ የሚሰብኩ መሆኑን በመናገር በተለይም ወጣቶች ስለሰላም አበክረን መስበክ ይጠበቅብናል ብሏል፡፡
ተሳታፊዎቹ ለሀገራችን ሰላምና እድገት ያለምንም ልዩነት እንሰራለን ብለዋል፡፡