ፋጭኤ - ቂምና ቁርሾ በመሻር ሰላምና አብሮነትን የሚያጸና! - ኢዜአ አማርኛ
ፋጭኤ - ቂምና ቁርሾ በመሻር ሰላምና አብሮነትን የሚያጸና!

በያንተስራ ወጋየሁ (ከኢዜአ ዲላ ቅርንጫፍ)
በቀደመው ትውልድ በማህበረሰቡ አልያም በግለሰብ የተፈጸመ በደል በይቅርታ ሳይሻር ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ ይመጣል። መሸጋገሩ ሳይበቃ ቂምና ቁርሾ ወልዶ ከተግባሩም ከታሪኩም በእጅጉ የራቀው የኋልኛው ትውልድ ጭምር ዋጋ ሲከፍልበት ማየት የተለመደ ነው።
በተለይ በነጠላ ትርክት በትውልድ ስነ ልቦና አሁን የተፈፀመ ያህል እንዲሰማ ተደርጎ መተረኩ በማህበረሰብ ትስስር ከዚያም ባለፈ በጋራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ላይም ከፍተኛ ጫና ሲያሳድር ቆይቷል። በዚህም አያሌ ሊቅና ደቂቅ ትልቁን ሀገራዊ ስዕል መመልከት ትተው በመንደርና በጎጥ ፖለቲካ ሲጠመዱና ሲሸጎጡ ይስተዋላል።
ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት የተፈጠሩ አለመግባባቶችንና በደሎችን በምክክር በመፍታት ጠንካራ ሀገራዊ አንድነትን ለመገንባት እየተሰራ ነው። ህብረ ብሔራዊነት የሰፈነበት ሀገረ መንግስት ግንባታን ለማጠናከርም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም ልዩነትን በምክክር ለመፍታትና የህዝቦችን አብሮነት ለማጠናከር እየተሰራ ነው።
ይህን ስራ ለማጠናከር የሚረዱ ባህላዊ ስርአቶችም በህብረተሰቡ ውስጥ አሉ። "ፋጭኤ" ለእዚህ አንድ ማሳያ ነው። በጌዴኦ ብሔር ተወላጆች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ቂምና ቁርሾ ማሻሪያ ባህላዊ ሥርአት ነው። የብሔሩ ተወላጆች ስርዓቱ ከማህበረሰብ እስክ ግለሰብ የደረሱ አለመግባባቶች፣ ቅሬታዎችና ያደሩ ቂምና ቁርሾዎችን በአግባቡ ለይቶ በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማውረድ ይጠቀሙበታል።
በሀገራችን በተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ የዳኝነትና የግጭት አፈታት ሥርዓቶች አሉ። በጌዴኦ ብሔር ያለው የግጭት መፍቻ ሥርአት "ጋፌ" ተብሎ ይጠራል።
ይሁንና የፋጭኤ ስርዓት ከባህላዊ የዳኝነትና የግጭት አፈታት በእጅጉ የሚለይና የሚልቅ እንደሆነ ይነገራል። በፋጭኤ ሥርአት በዳይ ተበዳይ ላይኖር ይችላል። በደሉ በየትኛውም ዘመን የተፈጠረ ቢሆንም በፋጭኤ ስርዓት ዋናው ነገር ሰላም ማውረድና ማህበራዊ ፍትህን ማረጋገጥ ነው።
በተለይ በደሉ ቂምና ቁርሾ ፈጥሮ ትውልድ እንዳይግባባ ካደረጋ የባህል ሽማግሌዎች በሶንጎ ተቀምጠው በደሉን በጥንቃቄ በመለየትና በማውገዝ ችግሩ በይቅርታ እንዲፈታ ያደርጋሉ።
ይህንን ሃሳብ የጌዴኦ ባህላዊ የባሌ አስተዳደር መሪ አባ ገዳ ቢፎሚ ዋቆ በተጨባጭ ምሳሌ ያስጠናክራሉ። ከመቶ ዓመታት በፊት "አኮ ማኖዬ" የተሰኝ በሴቶች የበላይነት የሚመራ ሥርዎ መንግስት ጌዴኦን ያስተዳድር ነበር።
ስርዓቱ ወንዶችን ይጨቁናል በሚልና በወንዶች በተቀነባበረ የውሸት ሴራ ንግስቲቱን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደልሥርዎ መንግስቱን እንዲገረሰስ ተደርጓል።
በወንዶች የተፈጸመው ይህ ጭካኔ የተሞላበት ግድያ ለብዙ መቶ ዓመታት በብሔሩ የስርዓተ ጾታ መስተጋብር ውስጥ የተዛባ ትርክት በመፍጠር በሴቶች ዘንድ ቂምና ቁርሾ እንዲቋጠር አድርጎ እንደነበር ነው አባ ገዳ ቢፎሚ የገለጹት።
እሳቸውን ጨምሮ የባህላዊ ስርዓቱ መሪዎች የባህላዊ ስርዓት መከወኛ ስፍራ በሆነው "ሶንጎ" ላይ ቁጭ ብለው በደሉን ገምግመውና መርምረው ችግሩን እንደለዩ አንስተዋል።
በወቅቱ የተፈጸመውን በደል ለህዝብ በማቅረብና የበደሉ ገፈት ቀማሽ የሆኑ ሴቶችን በአደባባይ ይቅርታ በመጠየቅ ቂምና ቁርሾ እንዲሽር ማድረጋቸውን ይናገራሉ። ይህም በዞኑ ሁለንተናዊ እድገትን ለማረጋገጥ የተባበረ አቅምን ለመጠቀም አስችሏል።
"ፋጭኤ ከቂምና ቁርሾ እንዲሁም ከበደል የመንጻት ባህላዊ ስርአት ነው" የሚሉት ደግሞ የሀገር በቀል እውቀቶች ተማራማሪው አቶ ፀጋዬ ታደሰ ናቸው።
እንደእሳቸው ገለጻ ስርአቱ በጌዴኦ ብሔር ተወላጆች ዘንድ በስፋት አዲስ ዓመት ከመሻገሩ በፊት የሚፈጸም የአንድነት ማጎልበቻ ስርዓት ነው። ፋጭኤ ከሰው ባለፈ ከፈጣሪም ጋር ሰላም የሚወርድበት ስርዓት መሆኑን ነው የሚናገሩት።
በተለይ ድርቅና ረሃብ ሲከሰት፣ ዝናብ በዝቶ ወንዝ ሙላት ህዝብን ሲያስችግር እንዲሁም ወረርሽኝ፣ ሰው ሰራሽ አደጋዎችና ጦርነት የህብረተሰቡን አኗኗር አደጋ ውስጥ ከጣሉ ፈጣሪ ተቆጥቷል በሚል የፋጭኤ ስርዐት ይከናወናል።
በዚህ ወቅት የባህላዊ ስርዓት መሪዎች (የሶንጐ አስተዳዳሪዎች) አካባባዊ ሁኔታን ገምግመው ህዝቡ ባህላዊ ክዋኔዎች በሚካሄድበት ስፍራ ወጥቶ በሰው፣ በእንስሳትና በተፈጥሮ ላይ ያደረሰውን በደል በመናዘዝ ይቅርታ እንዲጠይቅና ከፈጣሪው ጋር እንዲታረቅ የፋጭኤን ሥርዐት ያካሂዳሉ።
ይህም በህብረተሰቡ ውስጥ ሰላምና እርቅ እንዲወርድ ከማድረጉ ባለፈ ዛሬ ዞኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር የሚታወቅበት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እንዲጠናከር መሰረት መጣሉን እጩ ዶክተር ፀጋዬ ይገልጻሉ።
በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የባህል እሴቶችና የሀገር በቀል እውቀቶች መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ እስከዳር ግሩም በበኩላቸው እንዳሉት በኢትዮጵያ ፋጭኤን ጨምሮ ከ100 በላይ ሀገር በቀል እውቀቶች እንዳሉ ተለይተዋል። ይህም ኢትዮጵያን በባህል እሴቶች ተጠቃሽ እንደሚያደርጋት ነው የገለጹት።
ማህበረሰቡ በመኖር ሂደት ውስጥ ከተፈጥሮ ጋር ያለው ቁርኝት፣ የሚጠቀምባቸው የግጭት አፈታት ሥርዓቶች፣ የዘመን አቆጣጠር፣ የባህል ህክምናና የእድ ጥበብ ውጤት እንዲሁም የእርከንና የግብርና ልማት ሥራዎች ለሀገር በቀል እውቀቶች ተጠቃሽ ማሳያ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት ለሀገር በቀል እውቀትና እሳቤዎች ተገቢ ትኩረት መስጠቱ ባህላዊ እሴቶች እንዲበለጽጉ እድል ፈጥሯል። ለብሔራዊ የምክክር መድረኩም ተጨማሪ አቅም ያጎናጸፈና ልምድ እየሰጠ መምጣቱን ነው ያነሱት።
እነዚህ ባህላዊ እውቀቶች በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውሉና የአንዱ ባህል ለሌላው ተሞክሮ እንዲሆን ማስተዋወቅና ማስፋት ያስፈልጋል።
ለእዚህ ደግሞ የመገናኛ ብዙሀን ተቋማት ሚና የጎላ መሆኑን ነው የገለጹት። በማህበረሰቡ ዘንድ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉ በተለይም ለሀገራዊ አንድነትና ሰላም ፋይዳ ያላቸው ባህላዊ እሴቶች ከተደበቁበት ወጥተው እንዲተዋወቁ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ነው ወይዘሮ እስከዳር የተናገሩት።
በተለይ እንደ ፋጭኤ ያሉ ቂምና ቁርሾን በማስቀረት ለሰላምና ለህዝብች አብሮነት ዋጋቸው ከፍ ያሉ ባህላዊ ሥርአቶችን ማጎልበት፣ ማስተዋወቅና በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል የሁሉም ሃላፊነት መሆኑን ነው የገለጹት።