ቀጥታ፡

በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 32 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተመለሱ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 1/2017 (ኢዜአ)፦ መንግሥት በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 32 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሕንድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በማይናማር በእገታ ሥር ቆይተው ወደ ታይላንድ ከተሻገሩ 133 ኢትዮጵያ መካከል 32ቱ ዛሬ ወደ ሀገራቸው መግባታቸውንና 43 ኢትዮጵያውያንን ደግሞ ዛሬ ምሽት ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጿል።

ቀሪዎቹ በታይላንድ ማቆያ የሚገኙ 58 ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ ኤምባሲው ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አመልክቷል።

በተያያዘ መንግሥት ጃፓን በሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ወደ ታይላንድ በማሻገር ወደ አገራቸው ለመመለስ ጥረት እያደረገ ይገኛል።

መንግሥት ሕብረተሰቡ በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሀሰተኛ ቅስቀሳ ተታሎ የሥራ ስምሪት ውል ወደ አልተፈጸመባቸው አገራት ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዲቆጠብ ሚኒስቴሩ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም