የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመቄዶንያ የአረጋውያን እና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል 30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመቄዶንያ የአረጋውያን እና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል 30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 30/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመቄዶንያ የአረጋውያን እና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል 30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ እቤ ሳኖ 30ኛ ቀኑን በያዘው የመቄዶንያ የእርዳታ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ በመገኘት የባንኩን ድጋፍ አበርክተዋል።
አቶ አቤ እንዳሉት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች እና ማኔጅመንት አባላት የተሰበሰበ 18 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ባንኩ 12 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ በድምሩ 30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደርጓል።
አቶ አቤ መቄዶንያ እያከናወነ የሚገኘው የበጎ አድራጎት ስራ የሚደነቅ እና የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፣ ባንኩ እንደሁልጊዜው ሁሉ ከማእከሉ ጎን እንደሚቆም ተናግረዋል።
ሁሉም ዜጋ እንደየአቅሙ ለማዕከሉ ድጋፍ እንዲያደርግም አቶ አቤ ጥሪ ማቅረባቸውን የባንኩ መረጃ ያመለክታል።
የመቄዶንያ መስራች እና የበላይ ጠበቂ ቢኒያም በለጠ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመቄዶንያ ቋሚ ደጋፊ መሆኑን ገልጸው፣ በየጊዜው ለማዕከሉ ለሚያደርገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአሁኑን ድጋፍ ሳይጨምር ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት ለማዕከሉ ከ205 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉም በመረጃው ተጠቁሟል።