ቀጥታ፡

በ19ኛው አገር አቀፍ ፖሊስ ስፖርት ፌስቲቫል በተካሄደ ግማሽ ማራቶን ውድድር የኦሮሚያ ፖሊስ አትሌቶች አሸነፉ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 30/2017(ኢዜአ)፦ በ19ኛው አገር አቀፍ ፖሊስ ስፖርት ፌስቲቫል በተካሄደ ግማሽ ማራቶን ውድድር የኦሮሚያ ፖሊስ አትሌቶች ኮማንደር ታምራት ቶላ እና ምክትል ኮማንደር አትሌት ትግስት አሰፋ አሸንፈዋል።

በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አዘጋጅነት ከየካቲት 22 እስከ 30 ቀን 2017 ዓ.ም በተለያዩ የስፖርት ውድድሮች በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው 19ኛው አገር አቀፍ ፖሊስ ስፖርት ፌስቲቫል ማጠቃለያ ፕሮግራም በአዲስ አበባ ስታዲየም እየተካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎችም ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በመርሀ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ ዛሬ ማለዳ በተካሄደው የግማሽ ማራቶን በሁለቱም ጾታ የኦሮሚያ ፖሊስ አትሌቶች አሸንፈዋል።

በዚህም ወንዶች ግማሽ ማራቶን አትሌት ኮማንደር ታምራት ቶላ ከኦሮሚያ ፖሊስ 1ኛ፣ አትሌት ስማቸው ወልዴ ከአዲስ አበባ ፖሊስ 2ኛ፣ አትሌት ጫሉ ደሴ ከኦሮሚያ ፖሊስ 3ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

በሴቶች ግማሽ ማራቶን ምክትል ኮማንደር አትሌት ትግስት አሰፋ ከኦሮሚያ ፖሊስ፣ መሰለች አለማየሁ ከአዲስ አበባ ፖሊስ 2ኛ ፣ ሀመልማል ቢራራ ከአማራ ፖሊስ 3ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

የኢትጵያ ፖሊስ የተመሰረተበትን 116ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ እየተካሄደ የሚገኘው 19ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ሠራዊት ስፖርት ውድድር ፌዴራል ፖሊስ እና ኦሮሚያ ፖሊስ በአዲስ አበባ ስታዲየም በሚያደርጉት የእግር ኳስ ፍፃሜ ጨዋታ ይጠናቀቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም