ቀጥታ፡

የሴቶችን ተጠቃማነት በማሳደግ አካታችና ሁለንተዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላል

አመያ፤ የካቲት 30/2017 (ኢዜአ)፦ የሴቶችን ተጠቃማነት በማሳደግ አካታችና ሁለንተዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን “ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል” በሚል መሪ ሐሳብ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ደረጃ የፌደራል፣ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በኮንታ ዞን ተከብሯል።

የፌዴራል ከፍተኛ የሴት አመራሮች ቡድን በክልሉ ኮንታ ዞን በተለያዩ መዋቅሮች በሴቶች ልማት ማህበራት የተከናወኑ የተለያዩ የልማት ስራዎች ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

በዞኑ ሴቶች በግብርና በሰብልና በእንስሳት እንዲሁም በሌሎችም ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ተሰማርተው ውጤታማ መሆናቸውን ባደረጉት ምልከታ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ ዓሊ በዚሁ ወቅት፤ የሴቶችን ተጠቃማነት በማሳደግ አካታችና ሁለንተዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።


 

በሀገር ደረጃ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ኢንሼትቮች ተቀርፀው በርካታ ተግባት እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ከታች ጀምሮ በትኩረት መሠራት አለበት ብለዋል።

በምልከታው በክልሉ የተጀመሩ ስራዎች ሴቶችን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑናቸውን ማረጋገጣቸውንም እንዲሁ።

በሂደቱ የገጠሟቸው የብድር፣ የመስሪያና የመሸጫ ቦታ እንዲሁም የመንገድና ሌሎች ችግሮችን መፍታትና ድጋፍን አጠናክሮ መቀጠል በትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።

በሚኒስትር ማዕረግ የፌደሬሽን ምክርቤት የህገ-መንግስት ትርጉም ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ ወይዘሮ ፍሬሕይወት ዱባለ በበኩላቸው፣ የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በጉብኝት መከበሩ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።


 

በዞኑ በተጨባጭ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ውጤት እያመጡ እንደሆነ አንስተው፣ ይህም ይበልጥ እንዲጠናከር መደገፍና ውስንነቶችን ማረም ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ምስራቅ ማሞ፤ በመስክ ምልከታቸው የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ውጤት እያስገኙ መሆናቸውን አይተናል ብለዋል።


 

እነዚህ ጅምር ውጤቶች እየሰፉ እንዲሄዱ ተሞክሮን ቀምሮና አቅምን ለይቶ ማሰማራት እንዲሁም የተጠናከረ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ በማስገንዘብ።

ለሴቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት መረጋገጥ የአመራሩ ትኩረት ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግበዓቶች ልማት ድርጅት ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ አበባዬ ገዛሃኝ ናቸው።




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ገነት መኩሪያ በበኩላቸው፤ በክልሉ የሴቶችን ተጠቃሚነት በሁሉም መልኩ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው ብለዋል።




የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዐውደ ርዕይና በመስክ ጉብኝት መከበሩ፣ መሬት ላይ ያለውን ስራ በተጨባጭ ያሳየና በሂደትም ያጋጠሟቸውን ችግሮች በመለየት ለመፍታት ትልቅ እድል እየፈጠረ መሆኑንም ገልፀዋል።

የተሰጡ ግብረመልሶችን ወስዶ በተቀናጀ መልኩ በመፍታት የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን የማስፋትና ውጤታማነታቸውን የማሳደግ ስራ ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም