የመዲናዋ ወጣቶች ያላቸውን ዕምቅ አቅምና ክህሎት እንዲያዳብሩ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው - አቶ ሞገስ ባልቻ - ኢዜአ አማርኛ
የመዲናዋ ወጣቶች ያላቸውን ዕምቅ አቅምና ክህሎት እንዲያዳብሩ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው - አቶ ሞገስ ባልቻ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 30/2017(ኢዜአ)፦የመዲናዋ ወጣቶች ያላቸውን ዕምቅ አቅምና ክህሎት የሚያጎለብቱ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዲሞክራሲ ስርዓት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ ገለጹ።
ሰባተኛው ከተማ አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል "ብልጽግናና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አዘጋጅነት በሚሊኒየም አዳራሽ እየተካሄደ ይገኛል።
አቶ ሞገስ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የከተማው ወጣቶች ያላቸውን ዕምቅ አቅምና ክህሎት እንዲያዳብሩ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
ወጣቶች የነገ ሀገር ተረካቢ መሆን ብቻ ሳይሆን ዛሬ በሚሰሩ የልማት ስራዎች ላይ በንቃት የሚሳተፉ ትኩስ ኃይል መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ወጣቶች የራሳቸውን ክህሎትና ችሎታ መለየትና ማጎልበት የሚችሉበት በርካታ የስብዕና መገንቢያ ማዕከላት በመዲናዋ መገንባታቸውን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን በበኩላቸው፤ የፌስቲቫሉ ዓላማ አንድነት፣ ህብረ ብሄራዊነት፣ እህትማማችነትና ወንድማማችነትን በወጣቶች ዘንድ ይበልጥ ለማስረጽ ነው ብለዋል።
ከዚህም ባለፈም ወጣቶች የራሳቸውን ዕምቅ አቅም ለይተው በሀገር ልማትና ዘላዊ ሰላም ላይ የድርሻችውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻልና ያላቸው ልምድና ተሞክሮ የሚለዋወጡበት ነው ብለዋል።
በዛሬው ፌስቲቫል ላይ የሚወዳደሩ ወጣቶች በከተማው ስብዕና መገንቢያ ማዕከላት የነበሩ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ናቸው።