ቀጥታ፡

የሊጉ የ22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 30/2017 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ22ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።

ኢትዮጵያ ቡና ከሃዋሳ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

በሊጉ ኢትዮጵያ ቡና 32 ነጥብ በመሰብሰብ 2ኛ ደረጃን ይዟል።  ሃዋሳ ከተማ በ19 ነጥብ 15ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

ኢትዮጵያ ቡና የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ከሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ያለውን የነጥብ ልዩነት በጊዜያዊነት ወደ ሶስት ዝቅ ያደርጋል።

ሃዋሳ ከተማ ድል ከቀናው ከወራጅ ቀጠና የሚወጣበትን ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያገኛል።  

ቡድኖቹ በሊጉ የመጀመሪያ ዙር በነበራቸው ግንኙነት ኢትዮጵያ ቡና 3 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።  

ምሽት 12 ሰዓት ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከስሑል ሽሬ ይጫወታሉ።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ25 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።  ስሑል ሽሬ በ15 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ አቻ መለያየታቸው አይዘነጋም። 

የ22ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ መጋቢት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል። 

የደረጃ ሰንጠረዡን ኢትዮጵያ መድን በ38 ነጥብ እየመራ ነው። 

ኢትዮጵያ ቡና እና ሀዲያ ሆሳዕና በተመሳሳይ 32 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሁለተኛ እና ሶስተኛ  ደረጃን ይዘዋል። 

ሃዋሳ ከተማ፣ አዳማ ከተማ፣ ስሑል ሽሬ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ15ኛ እስከ 18ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

የአርባምንጭ ከተማው አህመድ ሁሴን በ10 ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራ ነው።

የመቀሌ 70 እንደርታው ያሬድ ብርሃኑ፣ የኢትዮጵያ ቡናው መስፍን ታፈሰ እና የሃዋሳ ከተማው ዓሊ ሱሌይማን በተመሳሳይ ስምንት ግቦች ይከተላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም