ቀጥታ፡

የባህል ስፖርቶችን ከመዝናኛነት ባለፈ ለአብሮነትና ለትስስር ማጎልበቻነት መጠቀም ይገባል- ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

ሆሳዕና ፡ የካቲት 29/2017(ኢዜአ) :- የባህል ስፖርቶችን ከመዝናኛነት ባለፈ ለአብሮነትና ለትስስር ማጎልበቻነት መጠቀም እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ ፡፡

22ኛው ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድርና 18ኛው የባህል ስፖርት ፌስቲቫል "ባህላዊ ስፖርታችን ለጠንካራ ህብረ-ብሄራዊ አንድነታችን" በሚል መሪ ሀሳብ በሆሳዕና ከተማ ዛሬ ተጀምሯል፡፡


 

ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)  በወቅቱ እንዳሉት የባህል ስፖርቶች በውስጣቸው የያዟቸው ዕሴቶች ከመዝነኛነት ባለፈ ለህዝቦች ትስስርና አብሮነት መጎልበት ያላቸው ሚና የላቀ በመሆኑ ልንጠቀምባቸው ይገባል፡፡

ስፖርት ከጤንነት በዘለለ ለወዳጅነት መጎልበትም ያለው ሚና የላቀ መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው (ዶ/ር)   በየአከባቢው ያሉ ባህላዊ የስፖርት ዘርፎች ለዚሁ ወሳኝ ማሳያዎች መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡

የህብረ-ብሄራዊ አንድነት መጠበቅና መረጋገጥ የባህል ስፖርቶችን አጉልቶ ለማሳየት ጠቃሚ መሆኑን ገልፀው የበለጠ እንዲጎለብትም መንግሥት ልዩ ትኩረት እንደሰጠው ተናግረዋል፡፡


 

በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መክዩ መሀመድ እንደተናገሩት ፡-ስፖርት የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በዘላቂነት በማጠናከር ረገድ ትልቁን ሚና ይጫወታል፡፡

ባህላዊ ስፖርቶች ያላቸውን አቅም ለመጠቀም የማልማትና የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

''በሀገሪቱ ከ293 በላይ ባህላዊ ስፖርቶች እንዳሉ በጥናት መለየቱን አንስተው የጨዋታ ህግና ስርዓት ተዘርግቶላቸው ለውድድር የበቁት ከ11 የስፖርት አይነቶች እንደማይበልጡና በቀጣይ ይህን ለማስፋት ይሰራል'' ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ የሚገኙ ባህላዊ ጨዋታዎችን በመደገፍና በማልማት ወደ ተዘውታሪ የስፖርት ዓይነት ለመቀየርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ህይወት መሀመድ በበኩላቸው ''የባህል ስፖርቶች ከመዝናኛነት ባለፈ ለቱሪዝም ዘርፍ ግብዓት በመሆን ያላቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው'' ብለዋል፡፡

የባህል ስፖርቶች የህብረ ብሄራዊ አንድነት እንዲጎለብት በማድረግ ለዘላቂ ሰላም መጠበቅና መረጋገጥ ከፍተኛውን ሚና እንደሚጫወቱ ገልፀዋል። 

ዛሬ ከሰዓት በሆሳዕና ከተማ የተጀመረው የባህል ስፖርት ውድድርና ፌስቲቫል ለተከታታይ 9 ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ 1 ሺህ 386 ስፖርተኞች ተሳትፎ እንደሚያደርጉም ታውቋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጣቶችና ስፖርት አማካሪ ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የክልል የስራ ኃላፊዎችና የሆሳዕናና አካባቢዋ የስፖርት ቤተሰቦች ተገኝተዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም