የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተሰማሩበት የሙያ መስክ በትጋት መስራት ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተሰማሩበት የሙያ መስክ በትጋት መስራት ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2017(ኢዜአ)፡- የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እርስበርስ መደጋገፍን ባህል ማድረግና በተሰማሩበት የሙያ መስክ በትጋት መስራት እንደሚያስፈልግ ስኬታማ ሴቶች ገለፁ።
የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኅብረት ከተባባሪ አካላት ጋር በመቀናጀት ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በውይይት አክብሯል።
በመድረኩ ስኬታማ ሴቶች የህይወት ልምዳቸውን ያጋሩ ሲሆን፤ በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ተወካዮች፣ ከትምህርት እና ከተለያዩ ተቋማት የተጋበዙ እንግዶች ተሳትፈዋል።
በመድረኩ ልምዳቸውን ያጋሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ መምህር ፕሮፌሰር የአለምፀሀይ መኮንን እንደገለጹት፤ በዓለም ላይ የስርዓተ ፆታ እኩልነት ጉዳይ ለረጅም ዘመናት ሲነገር ቢቆይም ፍሬ ለማፍራት በርካታ ዘመን ወስዷል።
ሴቶች ውጤታማ ለመሆን ባሉበት መስክ ስራቸውን በኃላፊነትና በትጋት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመው ሁሉም ህብረተሰብ ለሴቶች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ በተሰማሩበት መስክ ስኬታማ እንዲሆኑ ማስቻል ያስፈልጋል ብለዋል።
ተወዳዳሪ ለመሆን የራስ ጥረት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ ሴቶች ባሉበት መስክ ታታሪ መሆን እንዳለባቸውም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያን በተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉት አምባሳደር ገነት ዘውዴ በበኩላቸው፤ ሴቶች የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በማለፍ ውጤታማ ለመሆን ራሳቸውን በየጊዜው ማብቃት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ሴቶች እርስ በርሳቸው የሚተጋገዙበትና ልምዳቸውን የሚለዋወጡበት የትስስር መድረክ እንዲኖራቸውና ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀም እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ ዋና ዳይሬክተር አበራ ሀይለማርያም በበኩላቸው ኅብረቱ በተለይ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎን ማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
አርአያ የሆኑ ሴቶችን ታሪክ በመሰነድ ተደራሽ በማድረግና በመገናኛ ብዙሃን ስለ ሴቶች ተሳትፎ በማስገንዘብ የህብረተሰቡን ንቃተ ህሊና ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም አመልክተዋል።