ቀጥታ፡

የወንጀል ቅጣት አወሳሰን ረቂቅ መመሪያ ለተመሳሳይ ወንጀሎች ተቀራራቢ ውሰኔ ማሳለፍ የሚያስችል ነው - የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት

አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2017(ኢዜአ)፡- በወንጀል ቅጣት አወሳሰን ላይ የተዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተመሳሳይ ወንጀሎች ተቀራራቢ ውሳኔ ማሳለፍ የሚያስችል መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

በተሻሻለው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን ረቂቅ መመሪያ ላይ የቅጣት እርከን ያልነበራቸው የወንጀል አይነቶች መካተታቸውም ተገልጿል።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በወንጀል ቅጣት አወሳሰን ረቂቅ መመሪያ ላይ የክልልና ከተማ አስተዳደር የፍትሕ አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ የውይይት መድረክ አካሂዷል።


 

በዚሁ ጊዜ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፤ የተሻሻለው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን ረቂቅ መመሪያው የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

ረቂቅ መመሪያው በወንጀል ቅጣት ውሳኔ አሰጣጥ ሂደት የሚነሱ ቅሬታዎችን በመፍታት የወንጀል ሕጉን ግቦች ማሳካት በሚያስችል መልኩ ተገማች ውሳኔ ማስተላልፍ እንዲቻል መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ረቂቅ መመሪያው የቅጣት ደረጃና እርከን ያልነበራቸው ወንጀሎችን በማካተት በፍርድ ቤት የሚሰጡ ውሳኔዎች ተቀራራቢና አስተማሪ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም የቅጣት እርከን ያልወጣላቸው የወንጀል ድርጊቶች በዳኞች ፈቃደ ስልጣን ውሳኔ ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በተሻሻለው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን ረቂቅ መመሪያው ላይ በአስገድዶ መድፈር፣ በሰው መግደልና ሌሎች የወንጀል ድርጊቶች የቅጣት እርከን ከፍ እንዲሉ መደረጉን አብራርተዋል።

በዚህም ዳኞች ለተመሳሳይ የወንጀል ድርጊቶች ተቀራራቢ፣ ተገማችና ተዓማኒ ውሳኔ ማሳለፍ የሚያስችላቸው መሆኑን ገልጸዋል።


 

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንትና የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ዝግጅት ኮሚቴ ሰብሳቢ ተክሊት ይመሠል፤ በረቂቅ መመሪያው የቅጣት ደረጃ ያልነበራቸው ወንጀሎች የእርከን ደረጃ ወጥቶላቸዋል ብለዋል።

ረቂቅ መመሪያውም ለተመሳሳይ የወንጀል ድርጊቶች ተቀራራቢና ተገማች ውሳኔ በማሳለፍ የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን መሙላት በሚያስችል መልኩ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።


 

የአደገኛ መርዛማ መድኃኒቶች፣ የአደንዛዥ ዕፅ እና የጦር መሳሪያ ዝውውሮች፣ በቴሌኮምና ኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የቅጣት እርከን እንደወጣላቸው ገልጸዋል።

በተጨማሪም ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር፣ የታክስ ማጭበርበር ወንጀሎች ላይ የቅጣት እርከን መውጣቱ ፍርድ ቤቶች አስተማሪና ወጥ የቅጣት ውሳኔ እንዲያሳልፉ ያስችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም