ቀጥታ፡

አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ጥምረት እና የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ማህበር በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2017(ኢዜአ)፦አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ጥምረት እና የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ማህበር በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የአለም አቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ጥምረት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ኢትዮጵያ አለማየሁ እና የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ማህበር ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ድባቤ ባጫ ፈርመውታል።

የጥምረቱ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ኢትዮጵያ አለማየሁ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት ጥምረቱ ከ4 አመት በፊት በተለያዩ የአለም ክፍሎች በሚገኙ ሴት ኢትዮጵያውያን የተመሰረተ ነው።

በሀገር ውስጥ በተለያዩ  ምክንያቶች ችግሮች ሲያጋጥሙ ገንዘብ በማሰባሰብ ድጋፍ ማድረግ ጥምረቱ የተቋቋመበት ዋና አላማ ነው ብለዋል።

በዚህም ባለፉት 4 አመታት በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር ለተጋለጡ ሰዎች ከ20 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ልዩ ልዩ ድጋፎች ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በተለያየ የአለም ክፍሎች የሚኖሩ እና ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች መርዳት የሚያስችል አቅም ያላቸው የጥምረቱ አባላት እንዳሉም ተናግረዋል።

የዛሬው ስምምነት የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበርን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ መሆኑን በመግለጽ።

በዚህም ለአካል ጉዳተኞች እንቅስቃሴ የሚያግዙ ቁሳቁሶች እንደ ዊልቼር፣ ለአይነ ስውራን እንቅስቃሴ የሚረዳ በትር(ኬን) እና ብሬይል እንዲሁም መስማት ለተሳናቸው  የማዳመጫ ድጋፍ ማድረግን ያካትታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ማህበር ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ድባቤ ባጫ በበኩላቸው ማህበሩ በ4 ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች እንደሚሰራ ገልፀዋል።

ከአለም አቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ጥምረት ጋር የተደረገው ስምምነትም ሴት አካል ጉዳተኞችን በሚመለከቱ ጉዳዮች አብሮ መስራት የሚያስችል ነው ብለዋል። 

በዚህም የተለያየ የአካል ጉዳት ላለባቸው ሴቶች ልዩ ልዩ ድጋፎች ማድረግ የሚያስችል እንደሆነም ገልፀዋል።

በርካታ ሴት አካል ጉዳተኞች ለእንቅስቃሴ የሚረዱ ቁሳቁሶች የመግዛት አቅም በማጣት መማር እና መስራት እየቻሉ ከእንቅስቃሴ ተገድበው በሰው ድጋፍ ጥገኛ ሆነው የሚኖሩ እንዳሉ ጠቅሰዋል። 

ከጥምረቱ ጋር የተደረገው ስምምነትም ከተለያዩ የአለም ክፍሎች የሚገኙና የሰብአዊነት ስራ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ሴቶች የሚያደርጉትን ድጋፍ ያሳድጋል ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም