ቀጥታ፡

በሁሉም መስኮች የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲጠናከር መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ ነው-  ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) 

ሆሳዕና ፣የካቲት 29/2017 (ኢዜአ)፡- በሁሉም መስኮች የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲጠናከር በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን "ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች በመከበር ላይ ይገኛል።

በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳአና ከተማ በተከናወነው ሁነት ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲጠናከር መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የሴቶች ተሳትፎ ለእኩልነት፣ ለፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ወሳኝ መሆኑን በማንሳት በቀጣይ የተጠናከረ ጥረት ይደረጋል ብለዋል። 

በዚህ ረገድ በክልሉ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥሉ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አይሻ ያህያ፤ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመንግስት በርካታ አበረታች ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።


 

 

በዚህም ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ ገልጸው በሀገሪቷ እየተከናወኑ ባሉ የለውጥ ስራዎች ላይ ሴቶች ጠንካራ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።

የክልሉ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዘቢባ መሀመድናስር፤ በክልሉ ጠንካራ የሴቶች አደረጃጀት በመፍጠር በሁሉም ረገድ ሴቶች ተሳትፎ እንዲኖራቸው እየተደረገ ነው ብለዋል።


 

በፖለቲካ፣ በማህበራዊና የተለያዩ የልማት እንቅስቃሴ ላይ የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም