ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሴቶችን ለማብቃት የሚያከናውናቸው ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው - የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሴቶችን ለማብቃት የሚያከናውናቸው ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) ገለጹ።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀጣይነት ያለው የከፍታ ጉዞ ውስጥ የሴት ሙያተኞች ሚና የላቀ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ማርች 8 አስመልክቶ በየዓመቱ በሴቶች ብቻ የሚመራ በረራ ወደ ተለያዩ ከተሞች ያደርጋል።


 

ዘንድሮም ሙሉ በሙሉ በሴቶች ብቻ የሚመራ በረራ ወደ አቴንስ፣ ዴሊህ፣ ዱባይ፣ ዊንድሆክ እና ሳኦፖሎ ከተሞች አድርጓል።

በተጨማሪም ስድስተኛ መዳረሻውን በሀገር ውስጥ በሴቶች ብቻ የሚደረግ በረራ ወደ ባህር ዳር አድርጓል።

ለዚህ በሴቶች ብቻ ለሚመራው የበረራ ቡድን በአዲስ አበባ የሽኝት መርሃ-ግብር ትላንት ማታ ተከናውኗል።


 

በመርሃ-ግብሩ ላይ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)፣ የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሊዊጂ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ሃላፊ ለማ ያዴቻ፣ አትሌት መሰረት ደፋር፣ የአየር መንገዱ ሴት አመራር አባላት፤ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሴቶችን ለማብቃት የሚያከናውናቸው ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው።

በቀጣይም አየር መንገዱ ሴቶችን በአመራር ሰጪነትና በላቀ የሙያ ብቃት አስተዋጽኦቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሊያደርግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ሃላፊ ለማ ያዴቻ በበኩላቸው፤ አየር መንገዱ የሴቶችን ተሳትፎ በማበረታታት አካታች በሆነ መንገድ በርካታ ሴት አመራር አባላትና ባለሙያዎች ይዞ እየሰራ ይገኛል።

አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ አድማሱን እያሰፋ መሆኑን አመልክተው፤ የሴቶችን ሚናም በላቀ ድርሻ እየጨመረ መምጣቱን ገለጸዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀጣይነት ያለው የከፍታ ጉዞ የሴት ሙያተኞች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም