ሠራዊታችን ከፖለቲካ፣ ከዘርና ከሃይማኖት ወገንተኝነት የፀዳ የሠላም ሃይል ነው - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
ሠራዊታችን ከፖለቲካ፣ ከዘርና ከሃይማኖት ወገንተኝነት የፀዳ የሠላም ሃይል ነው - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2017(ኢዜአ)፦ሠራዊታችን ከፖለቲካ፣ ከዘርና ከሃይማኖት ወገንተኝነት የፀዳ የሠላም ሃይል ነው ሲሉ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ ለ3 ዓመት ያሰለጠናቸውን የ70ኛ ዙር ቃኘው ኮርስ እጩ መኮንን ሰልጣኞች በዲግሪ መረሃ ግብር አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት ከፍተኛ አካላዊና ሞራላዊ ጥንካሬን የሚጠይቀውን ከባዱን ፈተና በድል ተወጥታችሁ ለዚህ መብቃታችሁ ያላችሁን ቁርጠኝነትና ፅናታችሁን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ሀገራችን ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅና ካደጉት ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ የያዘችው የልማት ግስጋሴ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም ይህንን ለማደናቀፍ ከውስጥም ከውጭም ያሉ ፀረ_ሠላም ሃይሎች ያለ እረፍት በመስራት ላይ ይገኛሉ ሲሉ ገልጸዋል።
እድገትና ሰላማችንን የማይወዱ ባንዳዎችን የዛሬ ተመራቂ ሰልጣኞችም በአመራር ጥበብና ብቃት በመመርኮዝ መታገልና የቀቢፀ ተስፋቸውን ማጨልም ይገባችኋል ነው ያሉት።
ወታደራዊ አካዳሚው ከተቋሙ የሚሰጡትን ተልዕኮዎች በመቀበል በእውቀትና በክህሎት ብቁ አመራሮችን በማፍራት ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተወጣ ነው ብለዋል።
ሠራዊታችን ከማንኛውም ፖለቲካዊ ወገንተኝነት፣ ከዘርና ከሃይማኖት ወገንተኝነት የፀዳ ከህዝብ ወጥቶ ህዝቡን የሚያገለግል ታማኝ የህዝብ ልጅ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የዛሬ ጀማሪ የመኮነንነት ማዕረግ ለነገ ጄነራልነት መነሻ ነውና እችላለሁ በሚል መንፈስ መልካም አጋጣሚዎችን በመጠቀም ራሳችሁን ማብቃትና ለተልዕኮ በስነ ልቦናዊ ፅናት ለመሪነትና ለቴክኖሎጂ መስኮች መዘጋጀት አለባችሁ ሲሉ አሳስበዋል።
በመጨረሻም የአካዳሚው አመራሮችና አሰልጣኞች ለስልጠናው መሳካት ላሳዩት ቁርጠኝነት ምስጋና አቅርበዋል።
በስልጠና ቆይታቸው ብልጫ ውጤት ላመጡ ተመራቂዎች የዋንጫ፣ የወርቅ፣ የብርና የነሃስ ሽልማት በጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ መበርከቱን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።