ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ከካሜሮን ጋር ታደርጋለች  

አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ማጣሪያ ጨዋታን ዛሬ ከካሜሮን ጋር ያካሂዳል። 

የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ከምሽቱ 3 ሰዓት 60 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ኦሎምቤ ስታዲየም ይደረጋል።

በአሰልጣኝ ራውዳ አሊ የሚመራው ብሄራዊ ቡድን ለጨዋታው በሀገር ቤት ከየካቲት 13 እስከ 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዝግጅቱን አድርጓል።

ቡድኑ ከትናንት በስቲያ ወደ ካሜሮን በማቅናት ቀሪ ዝግጅቱን አከናውኗል። 

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ነገ ከሚያደርገው ጨዋታ አስቀድሞ የመጨረሻ ልምምዱን ጨዋታውን በሚያደርግበት ኦሌምቤ ስታዲየም ትናንት ማምሻውን ማድረጉን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ የማጣሪያውን የመልስ ጨዋታ መጋቢት 6 ቀን 2017 ዓ.ም በአበበ በቂላ ስታዲየም ታደርጋለች።

ብሄራዊ ቡድኑ በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ በመጨረሻው ዙር ከዩጋንዳ እና ኬንያ አሸናፊ ጋር ይጫወታል።

ኢትዮጵያ በመጀመሪያው ዙር ከዚምባቡዌ ጋር ጨዋታውን እንድታደርግ ብትደለደልም ዚምባቡዌ ራሷን ከውድድሩ ማግለሏን ተከትሎ በፎርፌ ለሁለተኛ ዙር ማለፏ አይዘነጋም።

ዘጠነኛው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ በሞሮኮ አዘጋጅነት በጥቅምት እና ህዳር ወር 2018 ዓ.ም ይደረጋል።

በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 24 ሀገራት ይሳተፋሉ። ከሞሮኮ ውጪ አፍሪካ አራት ሀገራትን የማሳተፍ ኮታ አላት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም