ረቂቅ የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ነባራዊ ሁኔታንና ፍትሃዊነትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተዘጋጅቷል - የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት - ኢዜአ አማርኛ
ረቂቅ የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ነባራዊ ሁኔታንና ፍትሃዊነትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተዘጋጅቷል - የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት

አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2017(ኢዜአ)፡- ረቂቅ የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ የወቅቱን ነባራዊ ሁኔታና ፍትሃዊነትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መዘጋጀቱን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት ገለፁ።
በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተዘጋጀው ረቂቅ የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ላይ ባለድርሻ አካላት ውይይት እያደረጉ ናቸው።
መመሪያው ከተዘጋጀባቸው ምክንያቶች መካከል ወቅቱንና የወንጀል ዓይነቱን ያገናዘበ የቅጣት እርከንና ቅጣት ላልወጣላቸው ወንጀሎች ቅጣት መጣል ይገኙበታል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረትእንደገለጹት፤ መመሪያው የዳኞች ፍቃድ ስልጣን ነባራዊ ሁኔታንና ፍትሃዊነትን በጠበቀ መልኩ እንዲተገበር የሚያደርግ ነው።
አሁን ላይ እየተተገበረ ያለው መመሪያ በ2002 ዓ/ም መውጣቱን አስታውሰው፤ መመሪያው ከስድስት ዓመታት በኋላ ማሻሻያ እየተደረገበት መምጣቱንና እስካሁን እየተተገበረ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህም ወቅቱን ያላገናዘበ የወንጀል ቅጣት እንዲጣል ከማድረግ ባለፈ የአፈፃፀም ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል ነው ያሉት።
በረቂቅ መመሪያው የዳኞች ፍቃድ ስልጣን በመርህና በመመሪያ ታግዞ ነፃነትንና ፍትሃዊነትን ባረጋገጠ መልኩ እንዲተገበር ያደርጋል ብለዋል።
በረቂቅ የወንጀል ቅጣት መመሪያው ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ጨምሮ የአስገድዶ መድፈር፣ የሰው መግደልና ሌሎች የቅጣት እርከኖች ከፍ እንዲሉ ተደርጓል።
በመመሪያው ቀደም ሲል የወንጀል ቅጣት ደረጃ ያልወጣላቸው ወንጀሎችም የቅጣት እርከን ደረጃ ወጥቶላቸዋል ብለዋል።
በዚህም አደገኛና መርዛማ መድሃኒቶችና አደንዛዥ ዕፅ ዝውውሮች፣ የቴሌኮሙኒኬሽንና የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች፣ የሙስና፣ የጦር መሳሪያ ዝውውርና ወታደራዊ ወንጀሎች የቅጣት እርከን ተጥሎባቸዋል።
ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር፣ የታክስ መሰወርና ማጭበርበር ወንጀሎችም በረቂቅ መመሪያው የቅጣት እርከን የተጣለባቸው ናቸው።
በረቂቅ የቅጣት አወሳሰን መመሪያው ውይይት ላይ የሁሉም ክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የፍትህ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።