ቀጥታ፡

ለስድስት ወራት የሚቆይ ሁለተኛው ዙር ሀገር አቀፍ የብክለት መግቻ ንቅናቄ ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2017(ኢዜአ)፡- ''ጽዱ ኢትዮጵያንና አረንጓዴ አሻራን ባህል ማድረግ'' በሚል መሪ ሀሳብ ለስድስት ወራት የሚቆይ ሀገር አቀፍ የብክለት መግቻ ንቅናቄ በቅርቡ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

ለሁለተኛ ዙር የሚካሄደው ንቅናቄ ህብረተሰቡ የአካባቢ ብክለት ዓይነቶችን ተረድቶ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሆነም ተገልጿል።

የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ አካባቢን መጠበቅና መንከባከብ የሁሉም ህብረተሰብ ሃላፊነት ነው።

ህብረተሰቡ የብክለት ዓይነቶችን በአግባቡ ለይቶ በመከላከል ረገድ የድርሻውን እንዲወጣ የግንዛቤ ስራዎች ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቅርቡ ይፋ በሚደረገውና ለስድስት ወራት በሚዘልቀው የብክለት መግቻ ንቅናቄ ብክለትን አስመልክቶ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።

የፕላስቲክ ብክለትን ለመከላከል እየወጣ ያለውን ህግ ተግባራዊ ለማድረግ ለአምራቹና ተጠቃሚው በቂ ግንዛቤ ማስያዝ ያስፈልጋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ የመጀመሪያው ወር ፕላስቲክ ብክለት ላይ እንደሚያተኩርም ገልጸዋል።

አደገኛ የሚባሉትን ጨምሮ በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍልና ተቋማት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የማሳወቅ ስራ ይሰራል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የድምጽ ብክለትን ከመከላከል አኳያ በርካታ ስራዎች እንደሚቀሩ ገልጸው ይህንንም ለማስተካከል ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን በስፋት እንደሚሰራ ነው ያመለከቱት።

ኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት ከማሳካት አንጻር የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸው፤ የአፈርና ውሃ ደህንነትና ጥበቃ ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማዳበር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ለተለያዩ በሽታዎች ዋነኛ መንስኤ የሆነውን የአየር ብክለት ለመከላከል ታዳሽ ሃይልን በስፋት መጠቀም ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት የአካባቢና ማህበራዊ ግምገማ ጥናት ሳያከናውኑ ፕሮጀክቶችን እንዳይጀምሩ የሚያደርገውን ህግ ተግባራዊ በማያደርጉ ፕሮጀክቶች ላይም ቅጣት እንደሚጣል ተናግረዋል።

ማንኛውም ፕሮጀክት የህብረተሰቡን ጤናና የአካባቢ ደህንነትን ያማከለ እንዲሆን በቂ የግንዛቤ ስራ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል።

''ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ'' በሚል መሪ ሃሳብ ከሚያዝያ 1 ቀን 2016 እስከ መስከረም 30 ቀን 2017 የመጀመሪያው ዙር ሀገር አቀፍ የብክለት መግቻ ንቅናቄ መካሄዱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም