ቀጥታ፡

ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎችን ስጋት የማይሆኑበት ደረጃ ለማድረስ የምርምር ስራዎች እየተከናወኑ ነው - የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2017(ኢዜአ)፡- ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎች የማህበረሰብ ስጋት የማይሆኑበት ደረጃ ለማድረስ የበሽታዎቹን ዝርያ መሰረት ያደረጉ ምርምሮች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎች በቫይረስ፣ በባክቴሪያና የተለያዩ ተህዋስያን አማካኝነት ይከሰታሉ፡፡

በአፈር ንክኪና በውሃ የሚተላለፉ፣ በትንኝ የሚመጡ እንደ ጊኒ ወርምና ትራኮማን የመሳሰሉት ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎች ናቸው፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት እኤአ ከ2021-2030 ያወጣው ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎች ፍኖተ ካርታ እንደሚያሳየው በዓለም ላይ ከ1 ቢሊየን በላይ ዜጎች ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ያሳድራሉ፡፡

ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎች ስትራቴጂክ እቅድ እስከ 2030 አብዛኞቹን የማጥፋትና የመከላከል ግብ አስቀምጣለች፡፡

በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባና ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎች ዳይሬክተር ዶክተር ገረመው ጣሰው ለኢዜአ እንዳሉት፤ ቆንጭር(ልሽማኒያስስ) እና የእንቅልፍ በሽታ(ትራፖኖማያስስ) ትኩረት የሚሹ የሐሩራማ በሽታዎች ናቸው፡፡

ኢንስቲትዩቱ ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በምርምር የተደገፉ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በሽታዎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚከናወኑ ምርምሮች የበሽታዎችን ዝርያ መለየትና መድኃኒቶችን ማቅረብ የሚያስችሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በዓለም አቀፍና በሀገር ደረጃ ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎች የማህበረሰብ ስጋት የማይሆኑበት ደረጃ ማድረስ እና ማጥፋት የሚያስችል እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሬቢስ(እብድ ውሻ በሽታን) ለመቆጣጠር ብሔራዊ የሬቢስ በሽታ ቁጥጥር ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2025 የጊኒ ወርም በሽታን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ታቅዶ እንደነበር አስታውሰው፤ ባለፉት ዓመታት በሽታው በሰዎች ላይ አልተገኘም ብለዋል፡፡

ወሰን ተሻጋሪ የሆኑ ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎችን ለመከላከል ከጎረቤት ሀገራት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም