ሴቶችን በሚዲያው ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ማጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ሴቶችን በሚዲያው ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ማጠናከር ይገባል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2017(ኢዜአ)፦ ሴቶችን በሚዲያው ዘርፍ ያላቸውን ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ለማጠናከር ባለድርሻ ተቋማት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አመራር እና ሰራተኞች በትኩረት ለሴቶች እና ለህጻናት ማህበር በመገኘት አለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ”ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል” በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ሁነቶች አክብሯል።
የባለሥልጣኑ የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዮናስ ፋንታዬ በወቅቱ እንዳሉት፤ ባለስልጣኑ የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
የዘንድሮውን ዓለማ አቀፍ የሴቶች ቀንን በትኩረት ሴቶች እና ህጻናት ማህበር በመገኘት ለማክበር የታሰበበት ዋና ዓላማ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ያሉ ሴቶችና ህፃናትን የሚደግፉ ማህበራትን የስራ እንቅስቃሴዎችን በማየት አብሮ በጋራ ለመስራት አላማ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
መገናኛ ብዙሃን ሴቶችን ጨምሮ ትኩረት የሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተሳትፎ ማረጋገጥ ላይ አበክረው እንዲሰሩ በማድረግ ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
የባለስልጣኑ የሴቶች ህጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ መሪ ስራ አስፈጻሚ ዱሬቲ ታደሰ በበኩላቸው፤ እንደተቋም የሴቶችን ቀን ስናከብር በተለይ ልዩ ትኩረት የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
የሴቶችን መብት በማስጠበቅ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ረገድ ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ማህበሩ የሴቶችና ህጻናት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ የተናገሩት ደግሞ
የትኩረት ሴቶች እና ህጻናት ማህበር መስራች እና ስራ አስኪያጅ ሲስተር አሳየች ይርጋ ናቸው፡፡
ሴቶች በተለይ አቅም እንዲኖራቸው ብቁ እንዲሆኑ ሁሉም ዜጋ ድጋፍ የሚፈልጉ ሴቶችን እና ህፃናትን በመደገፍ የበኩሉን ሀላፊነት ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
የባለሥልጣኑ አመራር እና ሰራተኞች በዓሉን ለማክበር ወደ ተቋማቸው በመምጣታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
የባለስልጣኑ አመራሮች እና ሰራተኞች በማህበሩ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ114ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ49ኛ ጊዜ በነገው ዕለት ይከበራል።