ሉዓላዊነታችንን የሚፈታተን የትኛውንም ኃይል እንደማንታገስ ጠላቶቻችን ያውቃሉ - ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ - ኢዜአ አማርኛ
ሉዓላዊነታችንን የሚፈታተን የትኛውንም ኃይል እንደማንታገስ ጠላቶቻችን ያውቃሉ - ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2017(ኢዜአ)፡- ሉዓላዊነታችንን የሚፈታተን የትኛውንም ኃይል እንደማንታገስ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጠንቅቀው ያውቁታል ሲሉ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ ተናገሩ።
ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ በሠራዊቱ የግዳጅ ቀጠና ተገኝተው ሠራዊቱን አበረታተው ወታደራዊ ዝግጁነቱን ተመልክተዋል።
በጀግኖች አባቶቻችን መስዋዕትነት የተረከብናትን ኢትዮጵያን የሚፈታተኑ ጠላቶቿን የማንበርከክና የማሸነፍ እቅሙም ብቃቱም እንዳለን እናንተ የዚህ ትውልድ ማሳያ ናችሁ ብለዋል።
ምንም አይነት ፈታኝ ሁኔታ የማይበግረን ጠንካራ ሠራዊት መሆናችንን ታሪካዊ ጠላቶቻችንም ይሁኑ ተላላኪ ባንዳዎቹ ያውቁታል ያሉት አዛዡ ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ ሠላም የምንከፍለው መስዋዕትነት የዚህ ትውልድ ደማቅ ታሪክ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ክቡር መስዋዕትነት ፀንታ ቀጥላለች ያሉት አዛዡ ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስ የሚጥር የትኛውም ኃይል ዋጋ ይከፍላል ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚዳፈር ብሎም የህዝባችንን ሠላም ለማደፍረስ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር የሚያብር የትኛውንም ተላላኪ ባንዳ አንታገስም ብለዋል።
እናንተ ለሠላም በከፈላችሁት ዋጋ የፅንፈኞች ህልም ከሽፏል ያሉት አዛዡ ወታደራዊ ዝግጁነታችሁ ለቀጣይ ተልዕኮ ያላችሁን ቁርጠኝነት ያሳያል ነው ያሉት።
እኛ ለአፍሪካውያን ብሎም ለመላው ጥቁር ህዝብ የአልደፈር ባይነትና የጀግንነት ተምሳሌት የሆነች የታላቅ ሀገር ሠራዊት ነን ሲሉም ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ መግጻቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ክብሯን ለማስጠበቅና ህገ-መንግስታዊ ተልዕኳችንን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የጀግንነታችን መሠረት የሆኑትን ወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ ከዕሴቶቻችንና ከህዝባዊ ባህሪያችን ጋር በማዋሃድ አጠናክረን መቀጠል አለብን ሲሉም አሳስበዋል።