ቀጥታ፡

በወልቂጤ ከተማ ሲካሄድ የቆየው 3ኛው ዙር የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ተጠናቀቀ

ወልቂጤ፤ የካቲት 28/2017(ኢዜአ)፡- በወልቂጤ ከተማ ሲካሄድ የቆየው 3ኛው ዙር የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ፍፃሜውን አገኘ።

3ኛው ዙር የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ፍፃሜውን ሲያገኝ በወንዶች ጋምቤላ ከተማ እንዲሁም በሴቶች ሀዋሳ ከተማ አሸናፊ ሆነዋል።

"ስፖርት ለሰላም፤ ለልማት፤ ለአንድነትና ለገፅታ ግንባታ" በሚል መሪ ሃሳብ በወልቂጤ ከተማ ከየካቲት 21/2017 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ውድድር ዛሬ ተጠናቋል።


 

የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ይመር ሀይሌ በወቅቱ እንዳሉት በውድድሩ የተጫዋቾች ጥራትና ብቃት ከመቼውም ጊዜ በላይ የተሻለ እንደነበር ገልጸዋል።

በስፖርተኞች መካከል የነበረው ተፎካካሪነት ለስፖርቱ እድገትና በቀጣይ ሀገራችን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎችን ለማግኘት ምቹ አጋጣሚ መሆኑንም አንስተዋል።

የወልቂጤ ከተማ ህብረተሰብ ውድድሩ ከተጀመረ አንስቶ በንቃት በመታደም ፍጹም በሆነ ጨዋነት ሲያበረታታ መቆየቱን ጠቅሰው የቅርጫት ኳስ ስፖርት በወልቂጤ ከተማ ባህል እየሆነ መምጣቱን ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ቅርጫት ኳስ አሰልጣኝ በላይነህ ችሎም በበኩላቸው ውድድሮቹ ተዘዋዋሪ መደረጋቸው ክለቦች ደጋፊ የሚያበዙበትን እና ተተኪዎች የሚፈሩበትን አጋጣሚ ፈጥሯል ነው ያሉት።


 

ሌላው የወልቂጤ ከተማ የሴቶች ቅርጫት ኳስ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ዘመዴ በቀለ ቡድናቸው ጥሩ ተፎካካሪ እንደነበር በመጠቆም ማህበረሰቡም የቅርጫት ኳስ ስፖርት ውድድሩን በንቃት መከታተሉን ገልፀዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ውድድሩ በከተማው እንዲከናወን ወጪውን በመሸፈን ጭምር ላደረገው ትብብርም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም