የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሙሉ በሙሉ በሴቶች ብቻ የሚመራ በረራ ወደ አምስት ዓለም አቀፍ ከተሞች ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሙሉ በሙሉ በሴቶች ብቻ የሚመራ በረራ ወደ አምስት ዓለም አቀፍ ከተሞች ያደርጋል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን አስመልክቶ ሙሉ በሙሉ በሴቶች ብቻ የሚመራ በረራ ዛሬ ማታ ወደ አቴንስ፣ ዴልሂ ፣ዱባይ፣ ዊንድሆክ እና ሳኦ ፖሎ ከተሞች እንደሚደረግ ነው አየር መንገዱ የገለጸው።
በተጨማሪም ከሃገር ውስጥ በሴቶች ብቻ የሚደረግ በረራ ወደ ባህር ዳር ያቀናል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን ማርች 8 አስመልክቶ በየዓመቱ በሴቶች ብቻ የሚመራ በረራ የሚያደርግ ሲሆን ዘንድሮም ለዘጠነኛ ጊዜ ለሚጓዙ ሴት የበረራ ሠራተኞች በአዲስ አበባ የሽኝት መረሃ-ግብር እየተካሄደ ይገኛል።
በመረሃ-ግብሩ ላይ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ሃላፊ ለማ ያዴቻ፣ አትሌት መሰረት ደፋር፣ የአየር መንገዱ አመራሮች፤ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ሃላፊ ለማ ያዴቻ በዚሁ ወቅት አየር መንገዱ የሴቶችን ተሳትፎ በማበረታታት አካታች በሆነ መንገድ በርካታ ሴት አመራሮችና ባለሙያዎችን ይዞ እየሰራ ይገኛል ብለዋል::
አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ አድማሱን እያሰፋ ባለበት ወቅት የሴቶች ሚና በላቀ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
በመጪው የአየር መንገዱ የልህቀት ጉዞም ሴቶች የመጪው ጊዜ የአቪዬሽን ሙያተኞች ሆነው እንዲቀጥሉ ያላሰለሰ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
በዚህም አየር መንገዱ የሴቶችን ተሳትፎ በማስቀጠል ሁሉን አቀፍ እድገት ለማረጋገጥ ይተጋል ነው ያሉት።
ሙሉ በሙሉ በሴቶች ብቻ የሚመራው ይህ በረራ ከዚህ ቀደም ወደ ባንኮክ፣ ኪጋሊ፣ ሌጎስ፣ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ኖርዌይ፣ ቦነስ አይረስ ዛንዚባር እና እንግሊዝ ጋትዊክ መጓዙ ይታወሳል።
በዛሬ በረራዎችም ዋና አብራሪዎች፣ፈርስት ኦፊሰሮች፣ የመስተንግዶ ባለሙያዎች እና ቴክኒሻኖች ሁሉም ሴቶች መሆናቸው ታውቋል።