ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችሉ ተጨባጭ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው - ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችሉ ተጨባጭ እርምጃዎች እየወሰደች እንደምትገኝ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የአየር ንብረት ፎረም ተቋቁሟል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና ለተፅዕኖዎች የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ተጨባጭ እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች።


 

ለዚህም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ልማት፣ የታዳሽ ኃይል አማራጭን መጠቀምና የአየር ብክለትን የመቀነስ ስራዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል።

መንግስት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ፖሊሲ እና ስትራቴጂዎችን ቀርጾ እየተገበረ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግዳሮት ሆኖ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት በጥናትና ምርምር ማገዝ እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ እያደረገቻቸው ያሉትን ጥረቶች ለዓለም በማሳወቅ በኩል መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ፋይናንስ ለማፈላለግ የሚደረገውን ድርድር ማገዝ እንደሚገባም ገልጸዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግዳሮት ሆኖ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፍልግ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እያደረገች ያለውን ስራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ማሳወቅ እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ እያደረገች ያለውን የድርድር አቅም የበለጠ ለማሳደግ ዩኒቨርሲቲዎች የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።

ዩኒቨርሰቲዎች የምሁራንን ተሳትፎ በማሳደግ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚያደርጉትን ጥናት እና ምርምር ማጠናከር እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።

ፎረሙ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ለዓለም ተሞክሮ የሆኑ ስራዎችን ማቅረብ፣ የሀገርን አቅም ማሳደግ እና በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንደሚገባው ተናግረዋል።


 

የትምህርት ሚኒስቴር ተወካይ ኤባ ሚጀና(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲዎች በአየር ንብረት ለውጥ ላይ እየተሰሩ ያሉ የጥናትና ምርምር ስራዎች ወደ ተግባር እንዲገቡና ለፖሊሲ ግብዓትነት እንዲውሉ መትጋት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።


 

የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች አመራር አባላት በበኩላቸው፤ የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል የሚያግዙ የተለያዩ ጥናትና ምርምሮች እንደሚያካሂዱ ገልጸዋል።


 

በቀጣይ ከመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በተጫማሪ ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ሀገራዊ ግብን ለማሳካት ቅንጅታዊ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም