የኢትዮጵያን ዕድገት ለማረጋገጥ የምርት ጥራትና የገበያ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ ይገባል - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ዕድገት ለማረጋገጥ የምርት ጥራትና የገበያ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ ይገባል - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያን ዕድገት ለማረጋገጥ የምርት ጥራትና ዘመናዊ የገበያ ተወዳዳሪነት አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት እና የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የበላይ ጠባቂ ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የሆራይዘን አዲስ ጎማ ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሥራ እንቅስቃሴን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም ሆራይዘን የተሽከርካሪ ጎማ ማምረቻ ፋብሪካ በሶስት ትውልዶች ቅብብሎሽ በምርት ጥራት፣ በአካባቢ ጥበቃና በዕውቀት ሽግግር ውጤታማ አቅም እየፈጠረ የመጣ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ፋብሪካው የስራ ባህልን በማሳደግ፣ የደንበኛ ፍላጎትን በመጠበቅና በተኪ ምርት ከዘመን ጋር በመጓዝ ለሀገር ዕድገት እያበረከተ ለሚገኘው የላቀ አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ለአምራችና አገልግሎት አቅራቢዎች ዕውቅና የሚሰጠው ሀገራዊ ፍላጎትና ዓላማን ታሳቢ አድርገው እንዲሰሩ ለማበረታታት ነውም ብለዋል።
የሽልማቱ ዋነኛ ዓላማ የኢትዮጵያን ምርትና አገልግሎቶች ጥራት በማሳደግ በአፍሪካና በዓለም ገበያ የተወዳዳሪነት አቅም እንዲገነቡ ለማስቻል መሆኑን ተናግረዋል።
የሆራይዘን አዲስ ጎማ ፋብሪካም በተኪ ምርት እያስመዘገበ ከሚገኘው ስኬት ባሻገር በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ለወጪ ንግድ ምርቶች ትኩረት መስጠት አለበት ብለዋል።
የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለቤት ሼህ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ለሀገር ዕድገት ለሚያበረክቱት አስተዋጽኦም ፕሬዝዳንት ታዬ ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዕድገት መሰረት የምርት ጥራትና የገበያ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ እና ተግቶ መስራት ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ለዚህም ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓትን መከተል ያስፍልጋል ብለዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ እንዳለው መኮንን፥ ጉብኝቱ የሆራይዘን አዲስ ጎማ ፋብሪካ የምርት ጥራት ተወዳዳሪነት ስርዓትን ለማየትና ለማበረታታት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለገበያ በማቅረብ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸውም ነው ያነሱት።
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቴዎድሮስ መብራት፥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የኢትዮጵያ ምርት እንዲኖራቸው ማስቻል የድርጅቱ ግብ መሆኑን ገልጸዋል።
በ11ኛው የጥራት ሽልማት ውድድር ከሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሆራይዘን አዲስ ብቸኛ ተወዳዳሪ እንደነበር አውስተው፤ ለ12ኛው የጥራት ውድድር 23 የግሩፑ ድርጅቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጀማል አህመድ፥ ለኢንዱስትሪ ተኪ ምርት የተሰጠው ትኩረት ሆራይዘን አዲስ ጎማ ፋብሪካ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለገበያ እንዲያቀርብ አስችሎታል ነው ያሉት።
በቀዳማዊ ኃይለ-ስላሴ ዘመነ መንግስት ጥቅምት 21/1965 ዓ.ም ስራ የጀመረው ሆራይዘን አዲስ ጎማ ፋብሪካ የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ባዘጋጀው 11ኛ ዙር ሀገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ውድድር የ1ኛ ደረጃ የልህቀት ዋንጫ ተሸላሚ መሆኑ ይታወሳል።