ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአል ሻባብ ይዞታዎች ላይ የአየር ድብደባ ፈጸመች

አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2017 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ደቡብ ምስራቃዊ ክፍል “ሚድል ሸበሌ” ግዛት በሚገኙ የአል ሻባብ ይዞታዎች ላይ የአየር ጥቃት ፈጽማለች።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በነበሩ የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮዎች የቡድኑን አቅም በከፍተኛ ሁኔታ በማዳከም ወሳኝ ሚና ተጫውታለች።

የአየር ጥቃቱ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በፀጥታ እና ደህንነት ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር የደረሱት ስምምነት አካል መሆኑ ተገልጿል።

የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር አብዱልቃድል መሐመድ ኑር የኢትዮጵያ ወታደራዊ ኃይል በ“ሚድል ሸበሌ” ግዛት በአል ሻባብ ይዞታዎች ላይ የአየር ጥቃት እንደፈጸመ መናገራቸውን ጋሮዌ ኦንላይንና ሶማሊ ጋርዲያን ዘግበውታል።

የአየር ጥቃቱ በሶማሊያ መንግስት ፈቃድ መፈጸሙን ገልጸው ይህም ሁለቱ ሀገራት በደህነነቱ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር እንደሚያመለክት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በአንካራው ስምምነት መሰረት በአል ሻባብ ላይ የጸረ-ሽብር እርምጃዎችን መውሰድን ጨምሮ በፀጥታ እና ደህንነት ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እየሰሩ ነው ብለዋል።

ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት በመከላከያ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር የሚያጠናክር ማዕቀፍ እንደሆነም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮ (አውሶም) እንዲሳተፍ በቅርቡ ከስምምነት ላይ መደረሳቸውን ሶማሊያ ጋርዲያን በዘገባው አስታውሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም በሶማሊያ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው ከሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሔክ መሐሙድ ጋር ውይይት አድርገዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት እና የሶማሊያ መንግስት ከውይይቱ በኋላ ባወጡት የጋራ መግለጫ ሀገራቱ የጋራ ጥቅምን ባከበረ መልኩ ትብብራቸውን ለማጠናከር መስማማታቸው የሚታወስ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለፉት ጥቂት ወራት የነበራቸውን ገንቢ ውይይቶች ተከትሎ የመጣ እና የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ነበረበት የመመለስን ስራ የሚያጠናክር ነው።

መሪዎቹ በሶማሊያ ብሔራዊ ወታደራዊ ኃይል እና በኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አዛዦች መካከል የደህንነት ትብብር ለማጠናከር እና ቀጣናዊ መረጋጋትን ለማስፈን ለደረሱበት የጋራ መግባባት እውቅና ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ተልዕኮ (አሚሶም) እና በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን በማሰማራት የአል ሻባብን አቅም በከፍተኛ በማዳከም በሶማሊያ የተሻለ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ወሳኝ ሚና ተጫውታለች።

የኢትዮጵያ እርምጃ የቡድኑ እኩይ አላማ ስር ሰዶ ከፍተኛ ጉዳት እንዳያደርስ ያደረገና የቡድኑን የተስፋፊነት መጥፎ ሕልም ያጨናገፈ ነበር።

ኢትዮጵያ ከተልዕኮዎቹ በተጨማሪ ከሶማሊያ ጋር በተፈራረመችው የሁለትዮሽ ስምምነት የሰላም አስከባሪዎቿን በማሰማራት ለሶማሊያ መረጋጋትና ደህንነት አስተዋጽኦ አድርጋለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም