በምርምር ማዕከላት የወጡ የተሻሻሉ የሰብልና የእንስሳት ዝርያዎችን ተደራሽ በማድረግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በምርምር ማዕከላት የወጡ የተሻሻሉ የሰብልና የእንስሳት ዝርያዎችን ተደራሽ በማድረግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል
ቡታጅራ፤ የካቲት 28/2017 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በግብርና ምርምር ማዕከላት የወጡ የተሻሻሉ የሰብልና የእንስሳት ዝርያዎችን ተደራሽ በማድረግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በምርምር ውጤቶችና በገጠሙ ማነቆዎች ላይ ለመምከር ያዘጋጀው መድረክ በቡታጅራ ከተማ ተካሂዷል።
በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ ግብርናን በማዘመን የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ለምርምር ሥራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።
በዚህም የተሻሻሉ የሰብልና የእንስሳት ዝርያዎችን የማፍለቅ፣ የማላመድና የማሰራጨት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በቴክኖሎጂ የታገዘና ገበያን መሰረት ያደረጉ የሰብልና እንስሳት ዘርፍ ልማቶችን በማከናውን የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ ነው ያነሱት።
በአንድ ዓመት ውስጥ በሰብል ዘርፍ ከ3 ሺህ 200 ኩንታል በላይ የስንዴ፣ ጤፍና ባቄላ የቅድመ መስራችና መስራች ዝርያዎችን በግብርና ምርምር ማዕከላቱ ተመርቶ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በእንስሳት ዘርፍም የወተትና ሥጋ ምርታማነትን ለማሳደግ ለእርባታ የሚሆኑ ከ3 ሺህ በላይ የዳልጋ ከብቶች ተሰራጭተዋል ብለዋል።
የወራቤ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ ቢላል ተመም እንዳሉት በእንስሳት ዘርፍ የበግ ኮርማ ዝርያ ማሻሻል ሥራ እንዲሁም በሰብል ዘርፍ ድርቅንና አሲዳማ መሬትን የሚቋቋሙ የባቄላ፣ ቅባት እህሎችና የሱፍ አበባ ዝርያዎችን የማላመድ ሥራ ተከናውኗል።
አሲዳማ አፈርን ተጽዕኖ መቋቋም የሚችል ጀጀቦ" የተሰኘ ስንዴ የማላመድ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም እንዲሁ።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀምድ ጀማል (ዶ/ር) የግብርና ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የምርምር ተቋማትን የማጠናከር ሥራ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው ጠቅሰዋል።
በክልሉ ግብርናውን በምርምር ለማገዝ የተጀመረው ሥራ አበረታች መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም ሥራውን አጠናክሮ ለማስቀጠል ባለድርሻ አካላትን አስተባብሮ መስራት እንደሚገባ ተናገረዋል።