ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ምርት ለማስተዋወቅና የንግድ ትስስርን ለመፍጠር ኢትዮ ቻምበር ዓለም አቀፍ ንግድ ትርዒቱ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያን ምርት ለማስተዋወቅና የንግድ ትስስርን ለመፍጠር ኢትዮ ቻምበር ዓለም አቀፍ ንግድ ትርዒት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

14ኛው ኢትዮ ቻምበር ዓለም አቀፍ ንግድ ትርዒት ከመጋቢት 4 እስከ 8 በአዲስ አበባ ኢግዚቢሽን ማዕከል ይካሄዳል።

የንግድ ትርዒቱን በተመለከተ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሀብረቢ በወቅቱ እንደገለጹት የፊታችን ሀሙስ በሚጀመረው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ዓለም አቀፍ የንግድ ተቋማት እና የሀገር ውስጥ ኢንተርፕራይዞች የሚሳተፉ ይሆናል።

የንግድ ትርዒቱ ለኢንዱስትሪ ልማት እድገት፣ ለስራ እድል ፈጠራ እና ለንግድ ስራ መስፋፋት የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች የሚቀርቡበት እንደሆነም ተናግረዋል።

በዓለም አቀፍ ተቋማትና በሀገር ውስጥ ኢንተርፕራይዞች መካከል የንግድ ትስስር ለመፍጠር ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።

በንግድ ዘርፉ እየተደረገ የሚገኘውን ሪፎርም በማስተዋወቅ በኩል ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ አንስተዋል።


 

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ቀነኒሳ ለሚ(ዶ/ር) በበኩላቸው ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ ከባቢ እንዲፈጠር የንግድ ትርዒቶች በተከታታይ እየተዘጋጁ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

14ኛው የኢትዮ ቻምበር ዓለም አቀፍ ንግድ ትርዒት 200 የሚደርሱ የቢዝነስ ተቋማትና ከ10 በላይ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚመጡ የቢዝነስ ተቋማት እንደሚሳተፉበት አስታውቀዋል።

የንግድ ትርዒቱ ህብረተሰቡ የራሱን ምርት እንዲጠቀም ለማበረታታት በማለም “የኢትዮጵያን ይግዙ” በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚካሄድም ተጠቅሷል።

የንግድ ትርዒቱ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እንዳዘጋጁትም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም