ቀጥታ፡

በከተማ አስተደደሩ ከሶስት ሺህ በላይ አባወራና እማወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮግራም ተጀመረ

ደብረማርቆስ፤ የካቲት 28/2017(ኢዜአ)- የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ከሶስት ሺህ በላይ አባወራና እማወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ዛሬ አስጀምሯል።

በፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሚሆኑት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሆኑ በማስጀመሪያው መርሃ ግብር ላይ ተገልጿል።


 

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ መንግስት የዜጎችን ኑሮ ደረጃ በማሻሻል ሀገራዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው።

በዚህም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በምግብ ዋስትና ፕሮግራም ታቅፈው ወደ ስራ በመግባት በሚያገኙት ገቢ የእለት ኑሯቸውን ከመሸፈን ባሻገር ቆጥበው ጥሪት  እንዲያፈሩ ሲሰራ መቆየቱን አውስተዋል።


 

ይህም በከተማ ፅዳትና ውበት፣ በተፋሰስና አረንጓዴ ልማት፣ በከተማ ግብርና እና በሌሎች የስራ ዘርፎች ላይ በማሰማራት  ብዙዎችን ውጤታማ ማደረግ እንደተቻለ ተናግረዋል።

ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከሶስት ሺህ በላይ አባወራና እማወራዎችን በመለየትና በፕሮግረሙ በማቀፍ የስራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል ነው ያሉት።


 

የከተማ አስተዳደሩ የምግብ ዋስትናና ሴፍቲኔት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ አየሁአለም አድማሱ በበኩላቸው፤ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በፕሮግራሙ ከዘጠኝ ሺህ 580 በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

ዛሬ በተጀመረው ሶስተኛው ዙር ፕሮግራም የታቀፉ ወገኖች ውጤታማ ተግባር እንዲያከናውኑ የሚያግዝ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መያዙን አመላክተዋል። 


 

በፕሮግራሙ ከታቀፉት መካከል አቶ ሃብታሙ መልኬ በሰጡት አስተያየት፤ በዚህ ስራ እንድሳተፍ መደረጉ መንግስት በቸገረኝ በትክክለኛው ወቅት እንደደረሰልኝ ነው የምረዳው ብለዋል።

ወይዘሮ ሽዋየ ታየ በበኩላቸው፤ የፕሮግራሙ ተጠቃሚ መሆኔ አስደስቶኛል ሲሉ ተናግረዋል።

በተመቻቸላቸው እድል በመጠቀም በቀጣይ ሰርተው ከሚያገኙት በመቆጠብ ኑሯቸውን በዘላቂነት ለመለወጥ እንደሚተጉ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም